1 Corinthians 10

በእስራኤል የደረሰው እንዳይደርስብን እንጠንቀቅ

1ወንድሞች ሆይ፤ አባቶቻችን ሁሉ ከደመናው በታች እንደ ነበሩና በባሕሩ ውስጥ እንደ ተሻገሩ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ። 2እነርሱ ሁሉ ከሙሴ ጋር ለመተባበር በደመናና በባሕር ተጠመቁ። 3ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ 4ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያ ዐለት ክርስቶስ ነበረ። 5ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በብዙዎቹ ደስ ስላልተሰኘ በበረሓ ወድቀው ቀሩ።

6እነርሱ ክፉ እንደ ተመኙ፣ እኛም ደግሞ እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆነውልናል። 7“ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ። 8ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሃያ ሦስት ሺሕ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም። 9ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑና በእባብ ተነድፈው እንደ ጠፉ፣ እኛም ጌታን አንፈታተን። 10ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጕረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጕረምርሙ።

11ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ። 12ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።

ከጣዖት ጋር አለመተባበር

14ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። 15ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ። 16የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? 17እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።

18እስቲ የእስራኤልን ሕዝብ አስቡ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን? 19ታዲያ፣ ለጣዖት የተሠዋ ነገርም ሆነ ጣዖቱ ራሱ ዋጋ ያለው ነገር ነው ማለቴ ነውን? 20አይደለም፤ አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ከአጋንንት ጋር እንድትተባበሩም አልሻም። 21የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም፤ ከጌታ ማእድና ከአጋንንት ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም። 22ጌታን እናስቀናውን? በብርታትስ ከእርሱ እንበልጣለንን?

የአማኞች ነጻነት

23“ሁሉ ነገር ተፈቅዷል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉም ነገር ተፈቅዷል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አያንጽም። 24እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ።

25በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ፣ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ 26ምድርና በውስጧ ያለው ሁሉ የጌታ ነውና።

27የማያምን ሰው ጋብዟችሁ ለመሄድ ብትፈልጉ በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ። 28ነገር ግን አንዱ፣ “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ፣ ይህን ስለ ነገራችሁ ሰውና ለኅሊናችሁ ስትሉ አትብሉ
አንዳንድ ቅጆች አትብሉ፤ “ምድርና በውስጧ ያለው ሁሉ የጌታ ናትና።”
29ይህን የምለውም ስለዚያ ሰው ኅሊና እንጂ ስለ አንተ አይደለም፤ ነጻነቴስ በሌላ ሰው ኅሊና ለምን ይመዘን? 30ምግቡን በምስጋና የምበላ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን ባመሰገንሁበት ነገር ለምን እወቀሣለሁ?

31እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። 32ለአይሁድም ሆነ ለግሪኮች ወይም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መሰናክል አትሁኑ፤ 33እኔ ሰውን ሁሉ በማንኛውም ረገድ ለማስደሰት እንደምጥር እናንተም እንዲሁ አድርጉ፤ ብዙዎችም ይድኑ ዘንድ፣ ለራሴ የሚጠቅመውን ሳይሆን ለእነርሱ የሚጠቅመውን እሻለሁና።

Copyright information for AmhNASV