2 Kings 8

የሱነማዪቱ ርስት ተመለሰ

1በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ፣ ልጇ ከሞት ያስነሣላትን ሴት፣ “እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የሰባት ዓመት ራብ ስለ ወሰነ፣ ተነሺና ለጊዜው መቈየት ወደምትችዪበት ቦታ ከቤተ ሰብሽ ጋር ሂጂ” አላት። 2ሴቲቱም ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገራት አደረገች፤ ከነቤተ ሰቧም ሄዳ፣ በፍልስጥኤም ምድር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።

3ከሰባት ዓመት በኋላም፣ ከፍልስጥኤም ምድር ተመልሳ መጣች፤ ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ አቤቱታ ለማቅረብም ወደ ንጉሡ ሄደች። 4በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው አገልጋይ ግያዝን፣ “ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ እስቲ ንገረኝ” እያለው ነበር። 5ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሣላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለማመልከት ወደ ንጉሡ ዘንድ የቀረበችውም፣ ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሣ ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ወቅት ነበር።

ግያዝም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ሴቲቱ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጇም ይህ ነው” አለ።
6ንጉሡም ስለ ስለዚሁ ጕዳይ ጠየቃትና ነገረችው።

ከዚያም ንጉሡ፣ “የነበራትን ሁሉ እንዲሁም ትታ ከሄደችበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ያለውን የዕርሻዋን ሰብል በሙሉ እንድትመልስላት” ሲል አንድ ሹም አዘዘላት።

አዛሄል ቤን ሃዳድን ገደለ

7ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ቤን ሃዳድ ታሞ ነበር፤ ለንጉሡም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቷል” ብለው ነገሩት። 8እርሱም አዛሄልን፣ “ገጸ በረከት ይዘህ ሂድና የእግዚአብሔርን ሰው ተገናኘው። በእርሱም አማካይነት፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው።

9አዛሄልም ደማስቆ ካፈራቻቸው ምርጥ ነገሮች ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ይዞ ኤልሳዕን ለመገናኘት ሄደ። ሄዶም ፊቱ ቆመና፣ “የሶርያ ንጉሥ ልጅህ ቤን ሃዳድ፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ሲል ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። 10ኤልሳዕም፣ “ሂድና፣ ‘መዳኑንስ በርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ነገር ግን እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል” ሲል መለሰለት። 11እስኪያፍር ድረስም፣ አዛሄልን ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው እንባውን አፈሰሰ።

12አዛሄልም፣ “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

ኤልሳዕም መልሶ፣ “በእስራኤላውያን ላይ የምታደርሰውን ጕዳት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ጕልማሶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናታቸውን በምድር ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ ያረገዙ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ” አለው።

13አዛሄልም፣ “ለመሆኑ እንደ ውሻ የሚቈጠር አገልጋይህ ይህን ጀብዱ መፈጸም እንዴት ይችላል?” አለ።

ኤልሳዕም መልሶ፣ “መቼም አንተ በሶርያ ላይ እንደምትነግሥ እግዚአብሔር አሳይቶኛል” አለው።

14ከዚያም አዛሄል ከኤልሳዕ ዘንድ ወጥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ ቤን ሃዳድም፣ “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ጠየቀው፤ አዛሄልም፣ “በርግጥ ከበሽታህ እንደምትድን ነግሮኛል” አለው። 15በማግስቱም ግን ወፍራም ልብስ ወስዶ በውሃ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም በዚሁ ሞተ፤ ከዚያም አዛሄል በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሆራም

8፥17-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 21፥5-10፡20 16የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮሆራም በይሁዳ ነገሠ። 17እርሱም ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። 18ያገባት የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች የአክዓብ ቤት እንደ አደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 19ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ሊያጠፋ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ለዳዊትና ለዘሩ መብራት እንደማያሳጣ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

20በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት፣ ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ። 21ስለዚህም ኢዮሆራም ሠረገሎቹን ሁሉ አሰልፎ ወደ ጸዒር ዘመተ። ኤዶማውያንም እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ከበቡ፤ እርሱና የሠረገላ አዛዦቹ ግን በሌሊት ተነሥተው ከበባውን ጥሰው ወጡ፤ ሰራዊቱም ሸሽቶ ተመለሰ። 22ኤዶምያስም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንደ ዐመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐምፆ ነበር። 23በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 24ኢዮሆራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እንደ እነርሱም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ

8፥25-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥1-6 25የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ በይሁዳ ነገሠ። 26አካዝያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሀያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ ጎቶልያ ትባላለች፤ እርሷም የእስራኤል ንጉሥ የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች። 27አካዝያስ ከአክዓብ ቤተ ሰብ ጋር በጋብቻ የተሳሰረ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንደ አደረገው ሁሉ፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

28አካዝያስም ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ በሶርያ ንጉሥ በአዛሄል ላይ ለመዝመት ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ፤ ሶርያውያንም በዚያ ኢዮራምን አቈሰሉት። 29ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም፣ በሬማት ከአዛሄል ጋር ባደረገው ጦርነት ሶርያውያን ካደረሱበት ቍስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ።

ከዚያም የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ስለ ታመመ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራሆም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

Copyright information for AmhNASV