2 Samuel 4

ኢያቡስቴ ተገደለ

1አበኔር በኬብሮን መሞቱን የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በሰማ ጊዜ ወኔ ከዳው፤ መላው እስራኤልም ደነገጠ። 2በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ የወራሪ ጭፍራ ቡድን መሪዎች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ አንዱ በዓና ሌላው ደግሞ ሬካብ ይባሉ ነበር። እነርሱም ከብንያም ነገድ የብኤሮት ተወላጅ የሆነው የሬሞን ልጆች ነበሩ፤ ብኤሮት ከብንያም ክፍል እንደ አንዱ ትቈጠራለች። 3የብኤሮት ሕዝብ ወደ ጌቴም በመሸሽ እስከ ዛሬም በመጻተኝነት እዚያው ይኖራልና።

4የሳኦል ልጅ ዮናታን ሁለት እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው። እርሱም የሳኦልና የዮናታን አሟሟት ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ። ሽባ የሆነውንም በዚህ ጊዜ ሞግዚቱ አንሥታው በጥድፊያ ስትሸሽ በመውደቁ ነው። ስሙም ሜምፊቦስቴ ይባል ነበር።

5በዚህ ጊዜ የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ወደ ኢያቡስቴ ቤት ለመሄድ ዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ፣ ሙቀት ሲሆን እኩለ ቀን ላይ ደረሱ፤ 6ስንዴ እንደሚፈልግም ሰው ሆነው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ሆዱ ላይ ወጉት። ከዚያም ሬካብና ወንድሙ በዓና ሹልክ ብለው ወጡ።

7ወደ ቤቱ ውስጥ የገቡት ኢያቡስቴ በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ተኝቶ ሳለ ነበር፤ ወግተው ከገደሉትም በኋላ ራሱን ቈርጠው በመውሰድ፣ ሌሊቱን ሁሉ በዓረባ መንገድ ተጓዙ። 8የኢያቡስቴንም ራስ ወደ ኬብሮን ዳዊት ዘንድ አምጥተው ንጉሡን፣ “አንተን ሊገድል ይፈልግ የነበረው የጠላትህ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ፤ እነሆ እግዚአብሔር በዛሬው ቀን ስለ ጌታዬ ስለ ንጉሡ ሳኦልንና ዘሩን ተበቅሏል” አሉት።

9ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞን ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን 10የምሥራች ያመጣልኝ መስሎት፣ ‘እነሆ ሳኦል ሞተ’ ብሎ የነገረኝን ሰው ይዤ ጺቅላግ ላይ ገደልሁት፤ እንግዲህ ለዚያ ሰው ስላመጣው ምሥራች የሸለምሁት ይህን ነበር። 11ታዲያ በገዛ ቤቱ፣ በገዛ ዐልጋው ላይ ዐርፎ የተኛውን ንጹሕ ሰው የገደሉትን ክፉ ሰዎች እንዴት የባሰ ቅጣት አይገባቸውም? ደሙን ከእጃችሁ መፈለግ፣ እናንተን ከምድሪቱ ማጥፋት የለብኝምን?”

12ስለዚህም ዳዊት የራሱን ሰዎች አዘዘ፤ እነርሱንም ገደሏቸው፤ እጅና እግራቸውንም ቈርጠው በኬብሮን ካለው ኵሬ አጠገብ ሰቀሏቸው። ነገር ግን የኢያቡስቴን ራስ ወስደው ኬብሮን በሚገኘው በአበኔር መቃብር አጠገብ ቀበሩት።

Copyright information for AmhNASV