Deuteronomy 27

በጌባል ተራራ ላይ የቆመ መሠዊያ

1ሙሴና የእስራኤል አለቆች ሕዝቡን እንዲህ ብለው አዘዙ፤ “ዛሬ የማዝዛችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ 2አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ጥቂት ትልልቅ ድንጋዮችን አቁምና በኖራ ቅባቸው። 3የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገር፣ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ጻፍባቸው። 4ዮርዳኖስን እንደ ተሻገርህም፣ ዛሬ ባዘዝሁህ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ ላይ ትከላቸው፤ በኖራም ቅባቸው። 5እዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የድንጋይ መሠዊያ ሥራ፤ በድንጋዮቹም ላይ ማናቸውንም የብረት መሣሪያ አታሳርፍባቸው። 6የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ካልተጠረበ ድንጋይ ሥራ፤ በላዩም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርብበት። 7በዚያም የኅብረት መሥዋዕት
በትውፊት የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል
ሠዋ፤ ብላም፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበልህ።
8በድንጋዮቹ ላይ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ግልጽ አድርገህ ጻፍባቸው።”

በጌባል ተራራ ላይ የተነገረ መርገም

9ሙሴና ሌዋውያን ካህናትም ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እስራኤል ሆይ፤ ጸጥ ብለህ አድምጥ! አንተ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሕዝብ ሆነሃል፤ 10አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ታዘዝ፤ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ጠብቅ።”

11ሙሴ በዚያኑ ዕለት ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዘ፦

12ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍና ብንያም ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ። 13ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳንና ንፍታሌምም በጌባል ተራራ ላይ ለመርገም ይቁሙ።

14ሌዋውያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ፦

15“የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራውን፣ በእግዘአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ የሆነውን ምስል የሚቀርጽ ወይም ጣዖትን የሚያበጅ፣ በስውርም የሚያቆም ሰው የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
16“አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን! ይበል።
17“የባልንጀራውን የድንበር ድንጋይ ከቦታው የሚያንቀሳቅስ የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
18“ዐይነ ስውሩን በተሳሳተ መንገድ የሚመራ፣ የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
19“በመጻተኛው፣ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
20“ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን፤ የአባቱን መኝታ ያረክሳልና።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
21“ከማናቸውም እንስሳ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርግ የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
22“የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ ከሆነችው እኅቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
23“ከዐማቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
24“በድብቅ ባልንጀራውን የሚገድል የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
25“ንጹሕን ሰው ለመግደል ጕቦ የሚቀበል የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
26“የዚህን ሕግ ቃሎች በመፈጸም የማይጸና የተረገመ ይሁን።”


ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
Copyright information for AmhNASV