Hosea 6

የእስራኤል ንስሓ አለመግባት

1“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤
እርሱ ሰባብሮናል፤
እርሱም ይጠግነናል፤
እርሱ አቍስሎናል፤
እርሱም ይፈውሰናል።
2ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤
በእርሱም ፊት እንድንኖር፣
በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል።
3 እግዚአብሔርን እንወቀው፤
የበለጠ እናውቀውም ዘንድ እንትጋ፤
እንደ ንጋት ብርሃን፣
በርግጥ ይገለጣል፤
ምድርን እንደሚያረሰርስ የበልግ ዝናብ፣
እንደ ክረምትም ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።”

4“ኤፍሬም ሆይ፤ ምን ላድርግህ?
ይሁዳ ሆይ፤ ምን ላድርግህ?
ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ጉም፣
እንደሚጠፋም የጧት ጤዛ ነው።
5ስለዚህ በነቢያቴ ቈራረጥኋችሁ፤
በአፌም ቃል ገደልኋችሁ፣
ፍርዴም እንደ መብረቅ በላያችሁ አበራ።
6ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣
ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እሻለሁና።
7እንደ አዳም
ወይም በአዳም እንደ ሆነው ወይም በሰዎች
ቃል ኪዳንን ተላለፉ፤
በዚያም ለእኔ ታማኝ አልነበሩም።
8ገለዓድ በደም የተበከለች፣
የክፉዎች ሰዎች ከተማ ናት።
9ወንበዴዎች ሰውን ለማጥቃት እንደሚያደቡ፣
ካህናትም በቡድን እንዲሁ ያደርጋሉ፤
በሴኬም መንገድ ላይ ሰዎችን ይገድላሉ፤
አሳፋሪም ወንጀል ይፈጽማሉ።
10በእስራኤል ቤት የሚሰቀጥጥ ነገር አይቻለሁ፤
በዚያ ኤፍሬም ዘማዊ ሆነ፤
እስራኤልም ረከሰ።

11“ይሁዳ ሆይ፤ ለአንተም፣
መከር ተመድቦብሃል።

“ሕዝቤን ከምርኮ አገር በመለስሁ ጊዜ፣
Copyright information for AmhNASV