Nehemiah 3

የቅጥሩ ሠራተኞች

1ሊቀ ካህናቱ ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ለሥራ ተነሡ፤ የበጎች በር የተባለውንም እንደ ገና ሠሩ። ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም በየቦታቸው ላይ አቆሙ። መቶ ማማ እስከሚባለው ግንብና ሐናንኤል ማማ ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ሠርተው ቀደሱት፤ 2ቀጥሎ ያለውንም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ እነርሱ ከሠሩት ቀጥሎ ደግሞ የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።

3የዓሣ በሩን የሃስናአ ልጆች ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።

4የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤ 5የሚቀጥለውን ክፍል የቴቁሐ ሰዎች መልሰው ሠሩ፤ መኳንንቶቻቸው ግን በተቈጣጣሪ አሠሪዎቻቸው
ጌቶቻቸው፤ ወይም ገዦቻቸው
ሥር ሆነው በሥራው መጠመድ አልፈለጉም።

6አሮጌውን
ወይም የይሻናን
በር የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም መልሰው ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ ማያያዣዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።
7ከእነርሱም ቀጥሎ የዕድሳቱ ሥራ የተከናወነው በኤፍራጥስ ማዶ በሚገኘው አገረ ገዥ ሥልጣን ሥር ባሉት በገባዖንና በምጽጳ ሰዎች በገባዖናዊው በመልጥያና በሜሮኖታዊው በያዶን ነበር። 8ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል የሚቀጥለውን ክፍል ሠራ፤ ከሽቱ ቀማሚዎች አንዱ የሆነው ሐናንያ ደግሞ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። እነርሱም “ሰፊው ቅጥር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ኢየሩሳሌምን መልሰው ሠሩ። 9ከዚያ የሚቀጥለውን ክፍል የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሆር ልጅ ረፋያ መልሶ ሠራ። 10የኤርማፍ ልጅ ይዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ፤ የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ ደግሞ ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። 11የካሪም ልጅ መልክያና የፈሐት ሞዓብ ልጅ አሱብ ሌላውን ክፍልና “የእቶን ግንብ” ተብሎ የሚጠራውን መልሰው ሠሩ። 12የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የአሎኤስ ልጅ ሰሎም ከሴት ልጆቹ ጋር በመሆን ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ።

13“የሸለቆ በር” ተብሎ የሚጠራውን የሐኖንና የዛኖ ነዋሪዎች ዐደሱት፤ መልሰው ሠሩት፤ ከሠሩትም በኋላ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጁ። እንዲሁም “የቈሻሻ መጣያ በር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን አንድ ሺሕ ክንድ
450 ሜትር ያህል ነው።
ቅጥር መልሰው ሠሩ።

14“የቈሻሻ መጣያ በር” ተብሎ የሚጠራው የቤት ሐካሪም አውራጃ ገዥ የሆነው የሬካብ ልጅ መልክያ መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራ በኋላም መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖረ።

15የምጽጳ አውራጃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም “የምንጭ በር” ተብሎ የሚጠራውን መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራም በኋላ ከድኖ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖረ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጀ። “የንጉሥ አትክልት ቦታ” ተብሎ በሚጠራው አጠገብ የሚገኘውን የሼላን መዋኛ ግንብም፣ ከዳዊት ከተማ ጀምሮ ቍልቍል እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ መልሶ ሠራ። 16ከእርሱም በኋላ የቤት ጹር አውራጃ እኩሌታ ገዥ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ እስከ ዳዊት መቃብር ትይዩ እስከ ሰው ሠራሹ ኵሬና “የጀግኖች ቤት” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን መልሶ ሠራ።

17ከእርሱ ቀጥሎ ሌዋውያኑ በባኒ ልጅ በሬሁ ሥር ሆነው የዕድሳት ሥራ ሠሩ። ከእርሱ ቀጥሎ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ ሐሸብያ አውራጃውን መልሶ ሠራ። 18ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ደግሞ የሌላው የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይና በእርሱም ሥር የነበሩት የአገሩ ሰዎች መልሰው ሠሩ። 19ከእርሱም ቀጥሎ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በሚያወጣውና እስከ ማእዘኑ በሚደርሰው ትይዩ ያለውን ሌላ ክፍል የምጽጳ ገዥ የኢያሱ ልጅ ኤጽር መልሶ ሠራ። 20ከእርሱም ቀጥሎ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማእዘኑ ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህኑ እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ያለውን ሌላ ክፍል በትጋት መልሶ ሠራ። 21ከእርሱ ቀጥሎ ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ያለውን ሌላ ክፍል የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት መልሶ ሠራ።

22ከእርሱም ቀጥሎ ያለውን ክፍል ከአካባቢው የመጡት ካህናት መልሰው ሠሩ። 23ከእነርሱ ቀጥሎ ብንያምና አሱብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን መልሰው ሠሩ፤ ከእነርሱም ቀጥሎ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን መልሶ ሠራ። 24ከእርሱም ቀጥሎ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማእዘኑና እስከ ማእዘኑም ጫፍ ያለውን ሌላውን ክፍል የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ መልሶ ሠራ፤ 25የኡዛይ ልጅ ፋላል ከቅጥሩ ማእዘን ትይዩና በዘብ መጠበቂያው አደባባይ አጠገብ ካለው ከላይኛው ቤተ መንግሥት መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱም ቀጥሎ የፋሮስ ልጅ ፈዳያና 26በዖፌል ኰረብታ ላይ የሚኖሩት የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች “የውሃ በር” ተብሎ ከሚጠራው ትይዩ ጀምሮ በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው ግንብ ድረስ መልሰው ሠሩ። 27ከእነርሱ ቀጥሎ የቴቁሐ ሰዎች ከታላቁ ግንብ ትይዩ ጀምሮ እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላ ክፍል መልሰው ሠሩ።

28“የፈረስ በር” ተብሎ ከሚጠራው በላይ ያለውን ደግሞ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየመኖሪያ ቤታቸው ትይዩ ያለውን መልሰው ሠሩ። 29ከእነርሱም ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን “የምሥራቅ በር” ጠባቂ የሆነው የሴኬንያ ልጅ ሸማያ መልሶ ሠራ። 30ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ሌላ ክፍል ደግሞ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛ ልጅ ሐኖን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የበራክያ ልጅ ሜሱላም ከመኖሪያው ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። 31ከእርሱ ቀጥሎ ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ መልክያ በመቈጣጠሪያው በር ትይዩ እስከሚገኘው እስከ ቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት፣ እንዲሁም ከማእዘኑ በላይ እስከሚገኘው ክፍል ያለውን መልሶ ሠራ፤ 32ከማእዘኑ በላይ ከሚገኘው ክፍል ጀምሮ እስከ በጎች በር ያለውን ደግሞ ወርቅ አንጥረኞቹና ነጋዴዎቹ መልሰው ሠሩ።

Copyright information for AmhNASV