Numbers 22

ባላቅ በለዓምን አስጠራ

1ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ወደ ሞዓብ ሜዳ ተጕዘው ከዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ከኢያሪኮ
በዕብራይስጥ የኢያሪኮ ዮርዳኖስ የሚባል ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ የጥንት ስም ሳይሆን አይቀርም።
ማዶ ሰፈሩ።
2በዚህ ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ፤ 3ሞዓብም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ተሸበረ፤ በርግጥም ሞዓብ በእስራኤላውያን ምክንያት በፍርሀት ተውጦ ነበር።

4ሞዓባውያንም የምድያምን ሽማግሌዎች፣ “በሬ የመስክ ሣር ጠራርጎ እንደሚበላ ሁሉ፣ ይህም ሰራዊት በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሏቸው።

ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፣
5ከወንዙ
የኤፍራጥስ ወንዝ ነው።
ዳር ባለች በትውልድ አገሩ በምትገኝ በፋቱራ የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እንዲጠሩት መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤

“እነሆ፤ ከብዛቱ የተነሣ ምድሩን የሸፈነ ሕዝብ ከግብፅ ወጥቶ በአቅራቢያዬ ሰፍሯል።
6ስለዚህ ይህን ሕዝብ መቋቋም ስለማልችል መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባትም ድል አድርጌ ከአገሪቱ ላስወጣቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ አንተ የምትባርከው ቡሩክ፣ የምትረግመውም ርጉም እንደሚሆን ዐውቃለሁና።”

7የሞዓብና የምድያም ሽማግሌዎችም ለሟርት የሚከፈለውን ዋጋ ይዘው ሄዱ፤ በለዓም ዘንድ በደረሱ ጊዜም የባላቅን መልእክት ነገሩት።

8በለዓምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጠኝን መልስ አመጣላችኋለሁና የዛሬን ሌሊት እዚሁ ዕደሩ” አላቸው። ስለዚህም የሞዓብ አለቆች ከእርሱ ዘንድ ቈዩ።

9እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “ከአንተ ጋር ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው።

10በለዓምም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንዲህ አለው፤ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን መልእክት ልኮብኛል፤ 11‘ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድሩን ገጽ አጥለቅልቆታል፤ ስለዚህ መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባት ልዋጋቸውና ላባርራቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል።’ ”

12 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን በለዓምን፣ “አብረሃቸው አትሂድ፤ የተባረከ ሕዝብ ስለ ሆነም አትርገመው” አለው።

13በማግስቱም ጧት በለዓም ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፣ “አብሬአችሁ እንዳልሄድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከልክሎኛልና እናንተ ወደ አገራችሁ ተመለሱ አላቸው።”

14ስለዚህ የሞዓብ አለቆች ወደ ባላቅ ተመልሰው፣ “በለዓም አብሮን ለመምጣት እንቢ አለን” አሉት።

15ከዚያም ባላቅ ከፊተኞቹ ይልቅ ቍጥራቸው የበዛና ይበልጥ የተከበሩ ሌሎች አለቆች ላከ። 16እነርሱም ወደ በለዓም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን እንድንነግርህ ልኮናል፤ ወደ እኔ ለመምጣት የሚያግድህ ምንም ነገር አይኑር፤ 17ወሮታህን በእጅጉ እከፍላለሁ፤ የምትለውንም ሁሉ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።”

18በለዓም ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ የአምላኬን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በመጣስ ከዚያ ያለፈ ወይም ያነሰ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አልችልም። 19አሁንም ሌሎቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እናንተም ዛሬ እዚሁ ዕደሩና እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን እንደሚለኝ ደግሞ ልወቅ።”

20በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች የመጡት እንድትሄድላቸው እስከ ሆነ ድረስ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ።”

የበለዓም አህያ

21በለዓም በጧት ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። 22ይሁን እንጂ በለዓም በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በጣም ተቈጥቶ ስለ ነበር የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ሊቃወመው በመንገዱ ላይ ቆመ። በለዓምም በአህያው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት አሽከሮቹም አብረው ነበሩ። 23አህያዪቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በመንገድ ላይ መቆሙን ባየች ጊዜ ከመንገድ ወጥታ ዕርሻ ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገዱ እንድትመለስ መታት።

24ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በሁለቱም በኩል ግንብ ባለበት በሁለት የወይን ተክል ቦታ መካከል በሚገኝ ጠባብ መተላለፊያ ላይ ቆመ። 25አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር አጣበቀችው፤ ስለዚህም እንደ ገና መታት።

26 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ ወደ ፊት ሄድ ብሎ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። 27አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ከበለዓም በታች ተኛች፤ በለዓም ተቈጥቶ ነበርና በበትሩ ደበደባት። 28ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የአህያዪቱን አፍ ከፈተ፤ በለዓምንም፣ “እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው።

29በለዓምም መልሶ አህያዪቱን፣ “ስላላገጥሽብኝ ነዋ! በእጄ ሰይፍ ይዤ ቢሆን ኖሮ አሁኑኑ በገደልሁሽ ነበር” አላት። 30አህያዪቱም ደግሞ በለዓምን እንዲህ አለችው፣ “ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተቀመጥህብኝ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ይህን የመሰለ ነገር የማድረግ ልማድ ነበረኝ?”

እርሱም፣ “በጭራሽ!” አላት።

31በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የበለዓምን ዐይን ከፈተ፤ እርሱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ እንደ ያዘ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ፤ ጐንበስ ብሎም በግንባሩ ተደፋ።

32 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ስለ ምንድን ነው? መንገድህ በፊቴ
የዚህ ጥገኛ ሐረግ የዕብራይስጡ ትርጕም አይታወቅም።
ጠማማ ስለሆነ ልቃወምህ መጥቻለሁ።
33አህያዪቱ አይታኝ ሦስቱንም ጊዜ ከፊቴ ዞር ባትልማ ኖሮ በእውነት እስካሁን አንተን በገደልሁህ፣ አህያዪቱን ግን በሕይወት በተውኋት ነበር።”

34በለዓምም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ እኔን ለመቃወም መንገዱ ላይ መቆምህን አላወቅሁም፤ አሁንም ደስ የማትሰኝ ከሆነ እመለሳለሁ” አለው።

35 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ በለዓምን፣ “መሄዱን ከሰዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው። ስለዚህ በለዓም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ።

36በለዓም በመምጣት ላይ መሆኑን ባላቅ በሰማ ጊዜ በግዛቱ ዳርቻ በአርኖን ወሰን ላይ ወደምትገኘው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊቀበለው ወጣ። 37ባላቅ በለዓምን፣ “በቶሎ እንድትመጣ ልኬብህ አልነበረምን? ለምን አልመጣህም? በርግጥ ወሮታህን ልከፍል የማልችል ሆኜ ነውን?” አለው።

38በለዓምም፣ “ይኸው አሁን መጥቻለሁ፤ ግን እንዲያው ማንኛውንም ነገር መናገር እችላለሁን? እኔ መናገር የሚገባኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በአፌ ያስቀመጠውን ብቻ ነው” ብሎ መለሰለት።

39ከዚያም በለዓም ከባላቅ ጋር ወደ ቂርያት ሐጾት ሄደ። 40ባላቅም ከብቶችና በጎች ሠዋ፤ ከፊሉንም ለበለዓምና ከእርሱ ጋር ለነበሩት አለቆች ሰጣቸው። 41በማግስቱም ጧት ባላቅ በለዓምን ወደ ባሞት በኣል አወጣው፤ እዚያም ሆኖ ሕዝቡን በከፊል አየ።

Copyright information for AmhNASV