Numbers 23

የመጀመሪያው የበለዓም ንግር

1በለዓም፣ “እዚህ ሰባት መሠዊያ ሥራልኝ፤ ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው። 2ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ ሁለቱም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።

3ከዚያም በለዓም ባላቅን፣ “እኔ ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ፤ ምናልባትም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊገናኘኝ ይመጣ ይሆናል፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው። ከዚያም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኰረብታ ሄደ።

4እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተገናኘው፤ በለዓምም፣ “እነሆ፤ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጅቻለሁ፤ በእያንዳንዱም ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቅርቤአለሁ” አለው።

5 እግዚአብሔርም (ያህዌ) በበለዓም አፍ መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመልሰህ ይህን መልእክት ንገረው” አለው።

6እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋር በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው። 7ከዚያም በለዓም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤

“ባላቅ ከአራም አመጣኝ፣
የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች።
‘ና ያዕቆብን ርገምልኝ፤
መጥተህም እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።
8እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያልረገመውን፣
እኔ እንዴት ረግማለሁ?
እግዚአብሔር (ያህዌ) ያላወገዘውንስ፣
እንዴት አወግዛለሁ?
9ከዐለታማ ተራሮች ጫፍ ሆኜ አየዋለሁ፤
በከፍታዎቹም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤
ተለይቶ የሚኖረውን፣
ራሱንም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የማይቈጥረውን ሕዝብ አያለሁ።
10የያዕቆብን ትቢያ ማን ቈጥሮ ይዘልቃል?
የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቈጥረዋል።
የጻድቁን ሞት እኔ ልሙት፤
ፍጻሜዬም የእርሱ ዐይነት ፍጻሜ ትሁን!”
11ባላቅም በለዓምን፣ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ አመጣሁህ፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አላደረግህልኝም!” አለው።

12እርሱም መልሶ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በአፌ ያስቀመጠውን መናገር አይገባኝምን?” አለው።

ሁለተኛው የበለዓም ንግር

13ከዚህ በኋላ ባላቅ፣ “እነርሱን ማየት ወደምትችልበት ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ፤ በእዚያም ሁሉን ሳይሆን በከፊል ብቻ ታያቸዋለህ፤ እዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ” አለው። 14ስለዚህም በፈስጋ ተራራ ጫፍ ላይ ወዳለው ወደ ጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ እዚያም ሰባት መሠዊያ ሠርቶ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።

15በለዓምም ባላቅን፣ “እርሱን ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ” አለው።

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) በለዓምን ተገናኘው፤ በአፉም መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመለስና ይህን መልእክት ንገረው” አለው።

17እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋር በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ ባላቅም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን አለ?” ሲል ጠየቀው።

18ከዚያም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤

“ባላቅ ሆይ ተነሣ፤ አድምጠኝ፤
የሴፎር ልጅ ሆይ ስማኝ፤
19ይዋሽ ዘንድ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰው አይደለም፤
ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፤
ተናግሮ አያደርገውምን?
ተስፋ ሰጥቶስ አይፈጽመውምን?
20እባርክ ዘንድ ትእዛዝ ተቀብያለሁ፤
እርሱ ባርኳል፤ እኔም ልለውጠው አልችልም።

21“በያዕቆብ መጥፎ ነገር አልተገኘም፤
በእስራኤልም
በያዕቆብ ላይ ወይም በእስራኤል ላይ እንከን አለማግኘቱን ያመለክታል።
ጕስቍልና አልታየም፤
እግዚአብሔር አምላኩ (ያህዌ ኤሎሂም) ከእርሱ ጋር ነው፤
የንጉሡም እልልታ በመካከላቸው ነው።
22እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከግብፅ አወጣቸው፤
ብርታታቸውም እንደ ጐሽ ብርታት ነው።
23በያዕቆብ ላይ የሚሠራ አስማት የለም፤
በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ሟርት አይኖርም፤
ለያዕቆብና ለእስራኤል፣
‘እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያደረገውን እዩ!’ ይባልላቸዋል።
24ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይነሣል፤
ያደነውን እስኪያነክት፣
የገደለውንም ደም እስኪጠጣ፣
እንደማያርፍ አንበሳ ሆኖ ይነሣል።”
25በዚህ ጊዜ ባላቅ በለዓምን፣ “እንግዲያውስ ፈጽሞ አትርገማቸው፤ ፈጽሞም አትመርቃቸው!” አለው።

26በለዓምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለኝን ሁሉ ማድረግ እንዳለብኝ አልነገርሁህምን?” ሲል መለሰለት።

ሦስተኛው የበለዓም ንግር

27ከዚህ በኋላ ባላቅ በለዓምን፣ “በል እንግዲያው ወደ ሌላ ቦታ ልውሰድህ፤ ከዚያ ሆነህ እንድትረግምልኝ ምናልባት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይፈቅድልህ ይሆናል” አለው። 28ባላቅም በለዓምን ምድረ በዳው ቍልቍል ወደሚታይበት ወደ ፌጎር ጫፍ አወጣው።

29በለዓምም፣ “ሰባት መሠዊያዎች እዚህ ሥራልኝ፤ ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው። 30ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።

Copyright information for AmhNASV