Numbers 24

1በለዓምም እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤልን መባረክ እንደ ወደደ ባየ ጊዜ፣ እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ አስማት ለመሻት አልሄደም፤ ነገር ግን ፊቱን ወደ ምድረ በዳ መለሰ። 2በለዓም አሻግሮ ተመልክቶ እስራኤል በየነገድ በየነገዱ ሆኖ መስፈሩን ሲያይ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መንፈስ በላዩ መጣበት፤ 3ንግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤

“የዚያ ዐይኑ የተከፈተለት፣
የቢዖር ልጅ የበለዓም ንግር፣
4የዚያ የአምላክን (ኤሎሂም) ቃል የሚሰማ፣
ሁሉን የሚችል
በዕብራይስጥ ሻዳይ ማለት ነው።
የአምላክን ራእይ የሚያይ፣
ከመሬት የተደፋው ዐይኖቹም የተከፈቱለት ሰው ንግር፤

5“ያዕቆብ ሆይ፤ ድንኳኖችህ፣
እስራኤል ሆይ፤ ማደሪያዎችህ እንዴት ያማሩ ናቸው!

6“እንደ ሸለቆዎች፣
በወንዝ ዳር እንዳሉም የአትክልት ስፍራዎች ተዘርግተዋል፤
በእግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተተከሉ ሬቶች፣
በውሃም አጠገብ እንዳሉ ዝግባዎች ናቸው።
7ከማድጋቸው ውሃ ይፈስሳል፤
ዘራቸውም የተትረፈረፈ ውሃ ያገኛል።

“ንጉሣቸው ከአጋግ ይልቃል፤
መንግሥታቸውም ከፍ ከፍ ይላል።

8“እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከግብፅ አወጣቸው፤
ብርታታቸውም እንደ ጐሽ ብርታት ነው፤
ጠላቶች የሆኗቸውን ሕዝብ ያነክታሉ፤
ዐጥንቶቻቸውን ያደቅቃሉ፤
በፍላጾቻቸው ይወጓቸዋል።
9እንደ አንበሳ አድፍጠዋል፤
እንደ እንስቲቱም አንበሳ አድብተዋል፤ ሊቀሰቅሳቸውስ የሚችል ማን ነው?

“የሚባርኩህ ቡሩክ፣
የሚረግሙህም ርጉም ይሁኑ።”
10ከዚያም ባላቅ፣ በበለዓም ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እጆቹንም አጨብጭቦ እንዲህ አለው፤ “ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፤ አንተ ግን ሦስቱንም ጊዜ ባረክሃቸው። 11በል ቶሎ ወደ ቤትህ ሂድልኝ፤ ወሮታህን አሳምሬ ልከፍልህ ነበር፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን እንዳታገኝ ከለከለህ።”

12በለዓምም ለባላቅ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ወደ እኔ ለላክሃቸው ሰዎች እንዲህ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን? 13‘ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለውን ብቻ ከመናገር በስተቀር ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ውጭ በራሴ ሐሳብ በጎም ሆነ ክፉ ማድረግ አልችልም።’ 14እንግዲህ ወደ ሕዝቤ እመለሳለሁ፤ ይሁን እንጂ በሚመጣው ዘመን ይህ ሕዝብ በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን ልንገርህ።”

አራተኛው የበለዓም ንግር

15ከዚያም እንዲህ ሲል ንግሩን ጀመረ፤

“የቢዖር ልጅ የበለዓም ንግር፤
የዚያ ዐይኑ የተከፈተለት ሰው ንግር።
16የዚያ የአምላክን (ኤሎሂም) ቃል የሚሰማ፣
ከልዑልም ዕውቀትን ያገኘው፣
ሁሉን ከሚችለው ራእይ የሚገለጥለት፣
መሬት የተደፋው፣ ዐይኖቹም የተገለጡለት ሰው ንግር፤

17“አየዋለሁ፤ አሁን ግን አይደለም፤
እመለከተዋለሁ፤ በቅርቡ ግን አይደለም፤
ኮከብ ከያዕቆብ ይወጣል፤
በትረ መንግሥት ከእስራኤል ይነሣል።
የሞዓብን ግንባሮች፣
የሤትንም ወንዶች ልጆች ራስ ቅል
የኦሪተ ሳምራውያኑ ቅጅ የራስ ቅል ሲል፣ በማሶሬቲክ ቅጅ ግን የቃሉ ትርጕም አይታወቅም።
ያደቅቃል።
18ኤዶም ይሸነፋል፤
ጠላቱ ሴይርም ድል ይሆናል፤
እስራኤል ግን እየበረታ ይሄዳል።
19ገዥ ከያዕቆብ ይወጣል፤
የተረፉትንም የከተማዪቱን ነዋሪዎች ይደመስሳል።”

የመጨረሻዎቹ የበለዓም ንግሮች

20ከዚያም በለዓም አማሌቅን አይቶ ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤

“አማሌቅ ከሕዝቦች የመጀመሪያው ነበር፤
በመጨረሻ ግን ይደመሰሳል።”
21ቄናውያንንም አይቶ ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤

“መኖሪያህ አስተማማኝ ነው፤
ጐጆህም በዐለት ውስጥ ተሠርቷል፤
22ያም ሆኖ ግን እናንት ቄናውያን፤
አሦር በምርኮ ሲወስዳችሁ ትደመሰሳላችሁ።”
23ከዚያም ንግሩን ቀጠለ፤

“አቤት! አምላክ (ኤሎሂም) ይህን
ሲያደርግ ማን ይተርፋል?
24መርከቦች ከኪቲም ዳርቻዎች
ይመጣሉ፤
አሦርንና ዔቦርን ይይዛሉ፤
እነርሱም ደግሞ ይደመሰሳሉ።”
25ከዚህ በኋላ በለዓም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ባላቅም መንገዱን ቀጠለ።

Copyright information for AmhNASV