Numbers 25

ሞዓብ እስራኤልን አሳሳተ

1እስራኤላውያን በሰጢም በነበሩበት ጊዜ ወንዶቹ ከሞዓብ ሴቶች ጋር ማመንዘር ጀመሩ። 2እነዚህም ሴቶች ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ሕዝቡን ጋበዙ፤ ሕዝቡም መሥዋዕቱን በላ፤ ለአማልክቱም ሰገደ።

3ስለዚህ እስራኤል የፌጎርን በኣል በማምለክ ተባበረ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ቍጣ በላዩ ነደደ።

4 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “አስፈሪው የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ ግደልና በጠራራ ፀሓይ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ስቀላቸው” አለው።

5ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች፣ “እያንዳንዳችሁ የፌጎርን በኣል በማምለክ የተባበሩትን ሰዎቻችሁን ግደሉ አላቸው።”

6ከዚህ በኋላ ሙሴና መላው የእስራኤል ማኅበር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ እያለቀሱ ሳለ፣ አንድ እስራኤላዊ እነርሱ እያዩት አንዲት ምድያማዊት ሴት ይዞ ወደ ቤተ ሰቡ መጣ። 7የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ይህን ባየ ጊዜ ማኅበሩን ትቶ ጦሩን በእጁ በመያዝ፣ 8እስራኤላዊውን ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ፤ ጦሩንም ወርውሮ እስራኤላዊውንና ሴቲቱን አጣምሮ ወጋቸው። ከዚያም በእስራኤላውያን ላይ የወረደው መቅሠፍት ተከለከለ፤ 9ሆኖም በመቅሠፍቱ የሞተው ሰው ቍጥር ሃያ አራት ሺሕ ደርሶ ነበር።

10 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 11“የካህኑ የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ እኔ ለክብሬ በመካከላቸው እንደምቀና ስለ ቀና ቍጣዬን ከእስራኤላውያን መልሶታል፤ ስለዚህ እኔም በቅናቴ ጨርሶ አላጠፋኋቸውም፤ 12ስለዚህ እነሆ እኔ የሰላም ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር እንደማደርግ ንገረው። 13ለአምላኩ (ኤሎሂም) ክብር ቀንቶ ለእስራኤላውያን ስላስተሰረየላቸው፣ እርሱና ልጆቹ ዘላቂ የክህነት ቃል ኪዳን ይኖራቸዋል።”

14ከምድያማዊቷ ሴት ጋር የተገደለው እስራኤላዊ የሰሉ ልጅ ዘንበሪ ይባላል፤ የስምዖናውያን ቤተ ሰብ አለቃ ነበር። 15እንዲሁም የተገደለችዋ ምድያማዊት ሴት ከስቢ ትባላለች፤ እርሷም ከምድያማውያን ቤተ ሰብ የአንዱ ነገድ አለቃ የሆነው የሱር ልጅ ነበረች።

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 17“ምድያማውያንን እንደ ጠላት ቈጥራችሁ ፍጇቸው። 18ይኸውም ፌጎር ላይ በተፈጸመው ድርጊትና በፌጎር ምክንያት በመጣው መቅሠፍት በተገደለችው በምድያማዊው አለቃ ልጅ፣ በእኅታቸው በከስቢ አታልለው የጠላትነት ሥራ ስለ ሠሩባችሁ ነው።”

Copyright information for AmhNASV