Psalms 26

የንጹሕ ሰው ጸሎት

የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ነቀፋ እንደ መሆኔ፣
አንተው ፍረድልኝ።
ወዲያ ወዲህ ሳልልም፣
በእግዚአብሔር ታምኛለሁ።
2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈትነኝ፤
መርምረኝም፤
ልቤንና ውስጤን መርምር፤
3ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየምና፣
በእውነትህም ተመላለስሁ።
4ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤
ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም።
5የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤
ከዐመፀኞችም ጋር አልቀመጥም።
6እጆቼን በየዋህነት እታጠባለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ መሠዊያህንም እዞራለሁ፤
7የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣
ታምራትህንም አወራ ዘንድ ነው።
8 እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣
የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ።

9ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋር፣
ሕይወቴንም ከደም አፍሳሾች ጋር አታስወግዳት።
10በእነርሱ እጅ የተንኰል ዕቅድ አለ፤
ቀኝ እጃቸውም ጕቦን ያጋብሳል።
11እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት እጓዛለሁ፤
አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ።

12እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤
በታላቅ ጉባኤ መካከልም እግዚአብሔርን እባርከዋለሁ።
Copyright information for AmhNASV