Psalms 51

የኀጢአት ኑዛዜ

ለመዘምራን አለቃ፤ ዳዊት ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ፣ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣
ምሕረት አድርግልኝ፤
እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣
መተላለፌን ደምስስ።
2በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤
ከኀጢአቴም አንጻኝ።

3እኔ መተላለፌን ዐውቃለሁና፤
ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው።
4በውሳኔህ ትክክል፣
በምትሰጠው ፍርድም ንጹሕ ትሆን ዘንድ፣
አንተን፣ በርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤
በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ።
5ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣
ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ።
6እነሆ፤ እውነትን ከሰው ልብ ትሻለህ፤
በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።

ስለዚህ ጥልቅ ጥበብን በውስጤ አስተምረኝ።
አስተምረህኛል ወይም ትፈልጋለህ ተብሎ መተርጐም ይቻላል።


7በሂሶጵ እርጨኝ፤ እኔም እነጻለሁ፤
ዕጠበኝ፤ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።
8ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤
ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው።
9ፊትህን ከኀጢአቴ መልስ፤
በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።

10አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤
ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
11ከፊትህ አትጣለኝ፤
ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።
12የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤
በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።
13እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤
ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
14የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤
ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤
አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል።
15ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤
አፌም ምስጋናህን ያውጃል።
16መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤
የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም።
17እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤
ወይም አምላክ ሆይ፤ የእኔ መሥዋዕት የተሰበረ

እግዚአብሔር ሆይ፤
አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።

18በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤
የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ።
19የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና
ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤
ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።
Copyright information for AmhNASV