Psalms 52

የክፉዎች ዕጣ ፈንታ

ለመዘምራን አለቃ፤ ኤዶማዊው ዶይቅ ወደ ሳኦል መጥቶ፣ “ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቷል” ብሎ በነገረው ጊዜ፤ የዳዊት
ርእሱ ምናልባት የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።
ትምህርት።

1ኀያል ሆይ፤ በክፋት ለምን ትኵራራለህ?
አንተ በእግዚአብሔር ዐይን የተናቅህ፣
እንዴትስ ዘወትር ትታበያለህ?
2አንተ ማታለልን ሥራዬ ብለህ የያዝህ፤
አንደበትህ እንደ ሰላ ምላጭ፣
ጥፋትን ያውጠነጥናል።
3ከበጎ ነገር ይልቅ ክፋትን፣
እውነትን ከመናገር ይልቅ ሐሰትን ወደድህ። ሴላ
4አንተ አታላይ አንደበት ሆይ፤
ጐጂ ቃላትን ሁሉ ወደድህ!

5እግዚአብሔር ግን ለዘላለም
ያንኰታኵትሃል፤
ይነጥቅሃል፤ ከድንኳንህም መንጥቆ ያወጣሃል፤
ከሕያዋንም ምድር ይነቅልሃል። ሴላ
6ጻድቃን ይህን አይተው ይፈራሉ፤
እንዲህ እያሉም ይሥቁበታል፤
7“እግዚአብሔርን መጠጊያ ያላደረገ፣
ነገር ግን በሀብቱ ብዛት የተመካ፣
በክፋቱም የበረታ፣
ያ ሰው እነሆ!”

8እኔ ግን በእግዚአብሔር ቤት፣
እንደ ለመለመ የወይራ ዛፍ ነኝ፤
ከዘላለም እስከ ዘላለም፣
በእግዚአብሔር ምሕረት እታመናለሁ።
9ስላደረግኸው ነገር ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፤
ስምህ መልካም ነውና፣ ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ፤
በቅዱሳንም መካከል አመሰግንሃለሁ።
Copyright information for AmhNASV