Psalms 68

ብሔራዊ የድል መዝሙር

ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር፤ ማሕሌት።

1እግዚአብሔር ይነሣ፤ ጠላቶቹ ይበተኑ፤
የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።
2ጢስ እንደሚበንን፣
እንዲሁ አብንናቸው።
ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፣
ክፉዎችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ።
3ጻድቃን ግን ደስ ይበላቸው፤
በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት ያድርጉ፤
ደስታንና ፍሥሓን የተሞሉ ይሁኑ።

4ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለስሙም ተቀኙ፤
በደመናት ላይ የሚሄደውን ከፍ አድርጉት፤
ወይም በምድረ በዳ ለሚሄደው መንገድን አዘጋጁለት።

ስሙ እግዚአብሔር በተባለው ፊት፣
እጅግ ደስ ይበላችሁ።
5እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣
ለድኻ ዐደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው።
6እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤተ ሰብ መካከል ያኖራል፤
ወይም ብቸኞችን በገዛ ምድራቸው

እስረኞችን ነጻ አውጥቶ ያስፈነድቃል፤
ዐመፀኞች ግን ምድረ በዳ ይኖራሉ።

7እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕዝብህ ፊት በወጣህ ጊዜ፣
በምድረ በዳም በተጓዝህ ጊዜ፣ ሴላ
8በሲና አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣
በእስራኤል አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣
ምድር ተንቀጠቀጠች፤
ሰማያትም ዶፍ አወረዱ።
9እግዚአብሔር ሆይ፣ በቂ ዝናብ አዘነብህ፤
ክው ብሎ የደረቀውን ርስትህን አረሰረስህ።
10መንጋህ መኖሪያው አደረጋት፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከበረከትህ ለድኾች ሰጠህ።

11ጌታ እንዲህ ሲል ቃሉን አስተላለፈ፤
ትእዛዙን የሚያውጁትም ብዙ ሰራዊት ናቸው፤
12“የሰራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤
በሰፈር የዋሉ ሴቶችም ምርኮን ተካፈሉ።
13በበጎች በረት መካከል
ወይም በኮርቻ ማስቀመጫዎች
ብትገኙ እንኳ፣
ከብር እንደ ተሠሩ የርግብ ክንፎች፣
በቅጠልያ ወርቅ እንደ ተለበጡ ላባዎች ናችሁ።”
14ሁሉን ቻዩ
ዕብራይስጡ ሻዳይ ይላል።
በዚያ የነበሩትን ነገሥታት በበተነ ጊዜ፣
በሰልሞን እንደሚወርድ በረዶ አደረጋቸው።

15አንተ ብርቱ ተራራ፣ የባሳን ተራራ ሆይ፤
አንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራራ፣ የባሳን ተራራ፤
16እናንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፤
እግዚአብሔር ሊኖርበት የመረጠውን ተራራ፣
በርግጥ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚኖርበትን ተራራ ለምን በቅናት ዐይን ታያላችሁ?
17የእግዚአብሔር ሠረገላዎች እልፍ አእላፍ ናቸው፤
ሺሕ ጊዜም ሺሕ ናቸው፤
ጌታ ከሲና ወደ መቅደሱ ገባ።
18ወደ ላይ ዐረግህ፤
ምርኮ አጋበስህ፤
እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ አንተ
ወይም እናንተ
በዚያ ትኖር ዘንድ፣
ከዐመፀኞችም ሳይቀር፣
ከሰዎች ስጦታን ተቀበልህ።

19ሸክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን፣
አዳኝ አምላካችን፣ ጌታ ይባረክ። ሴላ

20አምላካችን የሚያድን አምላክ ነው፤
ከሞት ማምለጥ የሚቻለውም በጌታ በእግዚአብሔር ነው።

21በርግጥ እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፣
በኀጢአታቸውም የሚጸኑትን ሰዎች ጠጕራም ዐናት ይፈነካክታል።
22ጌታ እንዲህ ይላል፤ “ከባሳን መልሼ አመጣቸዋለሁ፤
ከባሕርም ጥልቀት አውጥቼ አመጣቸዋለሁ፤
23እግርህ በጠላትህ ደም ውስጥ እንዲጠልቅ፣
የውሻህም ምላስ ከጠላትህ ድርሻውን እንዲያገኝ ነው።”

24አምላክ ሆይ፤ የክብር አካሄድህ ታየ፤
ይህም አምላኬና ንጉሤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያደርገው የክብር አካሄድ ነው።
25መዘምራን ከፊት፣ መሣሪያ የሚጫወቱ ከኋላ ሆነው ሲሄዱ፣
ከበሮ የሚመቱ ቈነጃጅትም በመካከላቸው ነበሩ።
26እግዚአብሔርን በጉባኤ አመስግኑት፤ ከእስራኤል ምንጭ የተገኛችሁ
እግዚአብሔርን አመስግኑ።
27የሚመራቸው ትንሹ ብንያም ነው፤
በዚያ በብዙ የሚቈጠሩ የይሁዳ መሳፍንት፣
እንዲሁም የዛብሎንና የንፍታሌም መሳፍንት ይገኛሉ።

28እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀይልህን እዘዝ፤
ብዙ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕምና የሱርስቱ ቅጅ እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀይልህን ጥራ ይላሉ። አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን እግዚአብሔር ለአንተ ኀይል ይጠራልሃል ይላሉ።

አምላክ ሆይ ቀድሞ እንዳደረግህልን አሁንም ብርታትህን አሳየን።
29በኢየሩሳሌም ስላለው ቤተ መቅደስህ፣
ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጡልሃል።
30በሸንበቆ መካከል ያሉትን አራዊት፣
በሕዝቡ ጥጆች መካከል ያለውንም የኰርማ መንጋ ገሥጽ፤
ብር ይገብር ዘንድም ይንበርከክ፤
ጦርነትን የሚወድዱ ሕዝቦችንም በትናቸው።
31መኳንንት ከግብፅ ይመጣሉ፤
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።

32የምድር መንግሥታት ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
ለጌታ ተቀኙ። ሴላ
33ከጥንት ጀምሮ ከነበሩት ሰማያት በላይ ለወጣው፣
በኀያል ድምፁ ለሚያስገመግመው ዘምሩ።
34ግርማው በእስራኤል ላይ፣
ኀይሉም ከደመናት በላይ ነው፣
እግዚአብሔርን ብርታት የአንተ ነው በሉት።
35እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በመቅደስህ ድንቅ ነህ፤
የእስራኤል አምላክ ለሕዝቡ ኀይልና ብርታትን ይሰጣል።

እግዚአብሔር ይባረክ!
Copyright information for AmhNASV