Revelation of John 10

መልአኩና ትንሿ መጽሐፍ

1ከዚህ በኋላ ሌላ ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ እርሱም በራሱ ላይ ቀስተ ደመና ነበር። ፊቱ እንደ ፀሓይ፣ እግሮቹ እንደ እሳት ዐምዶች ነበሩ። 2በእጁም የተከፈተች ትንሽ ጥቅልል መጽሐፍ ይዞ ነበር፤ ቀኝ እግሩን በባሕር ላይ፣ ግራ እግሩን በምድር ላይ አኖረ፤ 3እንደሚያገሣ አንበሳም ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ፤ በጮኸም ጊዜ የሰባቱ ነጐድጓዶች ድምፆች ተናገሩ። 4ሰባቱ ነጐድጓዶች በተናገሩ ጊዜ፣ ለመጻፍ ተዘጋጀሁ፤ ነገር ግን፣ “ሰባቱ ነጐድጓዶች የተናገሩትን በማኅተም ዝጋው እንጂ አትጻፍ” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማሁ።

5ከዚህ በኋላ በባሕርና በምድር ላይ ቆሞ ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሣ፤ 6እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚኖረው፣ ሰማይንና በውስጡ ያሉትን፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን፣ ባሕርንና በውስጡ ያሉትን በፈጠረው በእርሱ ማለ፤ እንዲህም አለ፤ “ከእንግዲህ መዘግየት አይኖርም፤ 7ነገር ግን ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋባቸው ቀኖች፣ ለአገልጋዮቹ ለነቢያት በገለጠላቸው መሠረት የእግዚአብሔር ምስጢር ይፈጸማል።”

8ከዚያም ከሰማይ የሰማሁት ድምፅ እንደ ገና እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ሂድ፤ በባሕርና በምድር ላይ ከቆመው መልአክ እጅ የተከፈተችውን ጥቅልል መጽሐፍ ውሰድ።”

9እኔም ወደ መልአኩ ሄጄ ትንሿን ጥቅልል መጽሐፍ እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት፤ እርሱም፣ “ውሰድና ብላት፤ ሆድህን መራራ ታደርገዋለች፤ በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች” አለኝ። 10ትንሿንም መጽሐፍ ከመልአኩ እጅ ተቀብዬ በላኋት፤ በአፌ እንደ ማር ጣፈጠች፤ ከበላኋት በኋላ ግን ሆዴ መራራ ሆነ፤ 11ከዚያም፣ “ስለ ብዙ ሕዝቦች፣ ወገኖች፣ ቋንቋዎችና ነገሥታት እንደ ገና ትንቢት ልትናገር ይገባሃል” ተባልሁ።

Copyright information for AmhNASV