Revelation of John 22

የሕይወት ወንዝ

1ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ መስተዋት የጠራውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤ 2ወንዙም በከተማዪቱ አውራ መንገድ መካከል ይፈስስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ። 3ከእንግዲህ ወዲህ ርግማን ከቶ አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማዪቱ ውስጥ ይሆናል፤ አገልጋዮቹም ያመልኩታል፤ 4ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በግንባራቸው ላይ ይሆናል። 5ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሓይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘላለም እስከ ዘላለምም ይነግሣሉ።

6መልአኩም፣ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኞች ናቸው። የነቢያት መናፍስት ጌታ አምላክ በቅርብ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ መልአኩን ልኳል” አለኝ።

ኢየሱስ ይመጣል

7 “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።”

8እነዚህን ነገሮች የሰማሁና ያየሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ። እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ላሳየኝ መልአክ ልሰግድ በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ 9እርሱ ግን፣ “ተው፤ ይህን አታድርግ እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት እንዲሁም የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁት ሁሉ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ” አለኝ።

10እንዲህም አለኝ፤ “ጊዜው ስለ ደረሰ፣ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፤ 11ዐመፀኛው በዐመፁ ይቀጥል፤ ርኩሱም ይርከስ፤ ጻድቁም ይጽደቅ፤ ቅዱሱም ይቀደስ።”

12 “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ። 13አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።

14 “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስና በበሮቿም በኩል ወደ ከተማዪቱ ለመግባት መብት እንዲኖራቸው ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። 15ውሾች፣ አስማተኞች፣ ሴሰኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸትን የሚወድዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።

16 “እኔ ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች እንዲመሰክር መልአኬን ለአብያተ ክርስቲያናት ልኬአለሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፣ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።”

17መንፈስና ሙሽራዪቱ፣ “ና” ይላሉ፤ የሚሰማም፣ “ና” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ።

18የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ቢጨምር፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ 19ማንም በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ከተጻፈው ቃል አንዳች ቢያጐድል፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ ዕድሉን ያጐድልበታል።

20እነዚህን ነገሮች የሚመሰክረው፣ “አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ” ይላል።

አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና።

21የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከእግዚአብሔር ሕዝብ
አንዳንድ ቅጆች …ከቅዱሳን ጋር ይሁን ይላሉ።
ጋር ይሁን፤ አሜን።
አንዳንድ ቅጆች አሜን የሚለውን አይጨምሩም።


Copyright information for AmhNASV