‏ 1 John 4

መናፍስትን መርምሩ

1ወዳጆች ሆይ፤ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። 2የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚቀበል መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ 3ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእግዚአብሔር አይደለም፤ እንደሚመጣ የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይህ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።

4ልጆች ሆይ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ እነርሱንም አሸንፋችኋቸዋል፤ ምክንያቱም በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል። 5እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ የሚናገሩት እንደ ዓለም ነው፤ ዓለምም ይሰማቸዋል። 6እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም፤ በዚህም የእውነትን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ እናውቃለን።

የእግዚአብሔር ፍቅርና የሰው ፍቅር

7ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። 8የማይወድድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። 9እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በእርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ። 10ፍቅር ይህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን እርሱ እንደ ወደደንና ስለ ኀጢአታችን ማስተስረያ
ወይም ኀጢአታችንን አስወግዶ፣ ቍጣውን ያርቅልን ዘንድ
ይሆን ዘንድ ልጁን መላኩ ነው።
11ወዳጆች ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ከወደደን፣ እኛም እርስ በእርሳችን መዋደድ ይገባናል። 12እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ ግን እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል።

13መንፈሱን ስለ ሰጠን፣ እኛ በእርሱ እንደምንኖር እርሱም በእኛ እንደሚኖር እናውቃለን። 14አብ ልጁን የዓለም አዳኝ ይሆን ዘንድ እንደ ላከው አይተናል፤ እንመሰክራለንም። 15ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምኖ በሚመሰክር ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። 16ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን።

እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።
17በዚህም ዓለም እርሱን እንመስላለንና፤ በፍርድ ቀን ድፍረት ይኖረን ዘንድ፣ ፍቅር በዚህ ዐይነት በመካከላችን ፍጹም ሆኗል፤ 18በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።

19እርሱ አስቀድሞ ወድዶናልና እኛ እንወድደዋለን። 20ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወድደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና። 21እርሱም “እግዚአብሔርን የሚወድድ ሁሉ ወንድሙን መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።

Copyright information for AmhNASV