‏ 1 Kings 13

ከይሁዳ የመጣ የእግዚአብሔር ሰው

1ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዞ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ። 2መሠዊያውንም በእግዚአብሔር ቃል በመቃወም እንዲህ አለ፤ “አንተ መሠዊያ ሆይ! እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እነሆ፤ ኢዮስያስ የተባለ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ እርሱም አሁን እዚህ መሥዋዕት የሚያቀርቡትን የኰረብታ ማምለኪያ ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ የሰዎችም ዐጥንት በአንተ ላይ ይነድዳል።’ ” 3በዚያች ዕለት ያ የእግዚአብሔር ሰው፣ እንዲህ ሲል ምልክት ሰጠ፤ “እግዚአብሔር የሰጠውም ምልክት፣ ‘እነሆ፣ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ላይ ያለው ዐመድ ይፈስሳል’ ” የሚል ነው።

4ንጉሥ ኢዮርብዓምም ያ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል መሠዊያ ላይ ጮኾ የተናገረውን ሲሰማ፣ እጁን መሠዊያው ካለበት በመዘርጋት፣ “ያዙት!” አለ፤ ነገር ግን ያች የዘረጋት እጁ ደርቃ ቀረች፤ ሊመልሳትም አልቻለም 5እንዲሁም ያ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ተመርቶ በሰጠው ምልክት መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ ዐመዱም ፈሰሰ።

6ከዚያም ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እጄ ወደ ቦታዋ እንድትመለስ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ለምንልኝ፤ ጸልይልኝም” አለው፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡ እጅ ወደ ቦታዋ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞዋም ሆነች።

7ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “አብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው።

8የእግዚአብሔር ሰው ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ አብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም። 9በእግዚአብሔር ቃል፤ ‘እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ ታዝዣለሁና።” 10ስለዚህም በመጣበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ቤቴል ተመለሰ።

11በዚያን ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም መጥተው በዚያች ዕለት የእግዚአብሔር ሰው እዚያ ያደረገውን ሁሉና ንጉሡንም ምን እንዳለው ለአባታቸው ነገሩት። 12አባታቸውም፣ “ለመሆኑ የተመለሰው በየትኛው መንገድ ነው?” በማለት ጠየቃቸው፤ ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የተመለሰበትን መንገድ ለአባታቸው አሳዩት። 13ስለዚህም ልጆቹን፣ “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነርሱም አህያውን ጫኑለትና ተቀምጦበት 14እየጋለበ ያን የእግዚአብሔር ሰው ተከተለው። ከዚያም በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘውና፣ “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።

እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።

15ስለዚህ ነቢዩ፣ “አብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው።

16የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ተመልሼ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ በዚህ ቦታም አብሬህ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤ 17‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዣለሁና” አለው።

18ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር። 19ስለዚህ የእግዚአብሔርም ሰው አብሮት ተመልሶ በቤቱ በላ፤ ጠጣም።

20በማእድ ተቀምጠው ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል መልሶ ወደ አመጣው ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤ 21ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃልለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዞች አልጠበቅህም፤ 22ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።

23የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፣ ያ መልሶ ያመጣው ነቢይ አህያውን ጫነለት። 24ሲሄድ ሳለም አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው ነበር። 25በዚያ ያለፉ ሰዎች ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳውም አጠገቡ ቆሞ ስላዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወዳለበት ከተማ ሄደው ይህንኑ ተናገሩ።

26ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን ሲሰማ፣ “ይህ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለለው ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ቃል መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ።

27ከዚያም ነቢዩ ልጆቹን፣ “በሉ አህያ ጫኑልኝ” አላቸውና ጫኑለት። 28ከዚያም ሄዶ ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ አንበሳውና አህያው በአጠገቡ ቆመው አገኘ፤ አንበሳው ሬሳውን አልበላውም፤ አህያውንም አልሰበረውም። 29ስለዚህ፣ ነቢዩ የዚያን የእግዚአብሔር ሰው ሬሳ አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነ፤ አልቅሶ ለመቅበርም ራሱ ወደሚኖርበት ከተማ አመጣው። 30ከዚያም ሬሳውን በራሱ መቃብር ቀበረው፤ “አወይ ወንድሜን” እያሉም አለቀሱለት።

31ከቀበሩትም በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “እኔም በምሞትበት ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ ዐጥንቶቼንም በዐጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ። 32በቤቴል ባለው መሠዊያ፣ በሰማርያ ከተሞችና በየኰረብታው ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል ጮኾ ያሰማው መልእክት በትክክል የሚፈጸም ነውና።”

33ይህም ሁሉ ሆኖ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገዱ አልተመለሰም፤ ይልቁንም በኰረብታ ማምለኪያዎች ከሁሉም የሕዝብ ክፍል እንደ ገና ካህናትን ይሾም ጀመር፤ ካህን ለመሆን የሚፈልገውንም ሁሉ ለየኰረብታ ማምለኪያዎቹ ለየ። 34ይህም ኀጢአት የኢዮርብዓም ቤት እንዲወድቅና ከምድር ገጽም እንዲደመሰስ ምክንያት ሆነ።

Copyright information for AmhNASV