1 Samuel 17
ዳዊትና ጎልያድ
1ፍልስጥኤማውያን ሰራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፣ በይሁዳ ምድር በሰኰት ላይ አከማቹ፤ እነርሱም በሰኰትና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌሰደሚም ሰፈሩ። 2ሳኦልና እስራኤላውያን ተሰብስበው፣ በዔላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ቦታ ቦታቸውን ያዙ። 3ሸለቆ በመካከላቸው ሆኖ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ኰረብታ እስራኤላውያን ደግሞ፣ ሌላውን ኰረብታ ያዙ።4ከጌት የመጣ ቁመቱ ከዘጠኝ ጫማ በላይ የሆነ፣ ጎልያድ የተባለ አንድ ጀግና ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ። 5እርሱም ከናስ የተሠራ የራስ ቍር ደፍቶ፣ ክብደቱ አምስት ሺሕ ሰቅል የሆነ የናስ ጥሩር ለብሶ ነበር። 6በእግሮቹ ላይ የናስ ገምባሌ አድርጎ፣ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናስ ጭሬ ይዞ ነበር። 7የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፣ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር።
8ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሰራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለ ምንድን ነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፣ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤ 9ከእኔ ጋር ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፣ እኛ ባሪያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባሪያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።” 10ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፣ “ዛሬ የእስራኤልን ሰራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ። 11ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም።
12ዳዊት በይሁዳ የቤተ ልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። 13ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤልያብ፣ ሁለተኛው አሚናዳብ፣ ሦስተኛውም ሣማ ይባላሉ፤ 14ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ 15ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር።
16ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጧትና ማታ ፊት ለፊት ብቅ እያለ ቆሞ ይታያቸው ነበር።
17በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ። 18ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለክፍል አዛዣቸው ▼
▼ዕብራይስጡ ሻለቃ ይላል።
አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደ ሆኑ አይተህ፣ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ። 19እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው በዔላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ናቸው።” 20ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፣ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጕዞ ጀመረ። ልክ ሰራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። 21እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። 22ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። 23ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ። 24እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሀት ከፊቱ ሸሹ።
25እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፣ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር።
26ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፣ “ለመሆኑ ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ።
27እነርሱም፣ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት።
28ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፣ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ፣ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው።
29ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልም?” አለ። 30ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፣ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ 31ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው።
32ዳዊትም ሳኦልን፣ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ ባሪያህ ሄዶ ይዋጋዋል” አለው።
33ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፣ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለሆነ፣ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው።
34ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፣ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፣ 35ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጕረሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። 36ባሪያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። 37ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።”
ሳኦልም፣ “ሂድ፤ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን” አለው።
38ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ጥሩር አጠለቀለት፤ ከናስ የተሠራ ቍርም ደፋለት። 39ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፣ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤
እርሱም ሳኦልን፣ “ያልተለማመድሁት ስለሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ሁሉንም አወለቀው። 40ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፣ ወንጭፉን በእጁ ይዞ፣ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ።
41ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። 42እርሱም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው። 43ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። 44እርሱም፣ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው።
45ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። 46እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቈርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፣ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል። 47እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።”
48ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፣ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። 49እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ፍልስጥኤማዊውም በግምባሩ ተደፋ።
50በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም።
51ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዝዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቈረጠው።
ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ። 52ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጌት መግቢያና እስከ ዔቅሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሸዓይራይም አንሥቶ እስከ ጌት ▼
▼አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን ሸለቆ ይላል።
ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወድቆ ነበር። 53እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሱ፤ ሰፈራቸውንም በዘበዙ። 54ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማዊውን የጦር መሣሪያዎች በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ። 55ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመግጠም በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ተመልክቶ የሰራዊቱን አዛዥ አበኔርን፣ “አበኔር ሆይ፤ ይህ ልጅ የማን ነው?” ሲል ጠየቀው።
አበኔርም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አላውቅም” ብሎ መለሰለት።
56ንጉሡም፣ “እንግዲህ ወጣቱ የማን ልጅ እንደ ሆነ ተከታትለህ ድረስበት” አለው።
57ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ እንደ ተመለሰ፣ አበኔር ይዞ ንጉሡ ዘንድ አቀረበው። በዚህ ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ በእጁ ይዞ ነበር።
58ሳኦልም፣ “አንተ ወጣት፣ የማን ልጅ ነህ?” ሲል ጠየቀው።
ዳዊትም፣ “እኔ የአገልጋይህ የቤተ ልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰ።
Copyright information for
AmhNASV