2 Chronicles 18
ሚካያ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ
18፥1-27 ተጓ ምብ – 1ነገ 22፥1-28 1ኢዮሣፍጥ ታላቅ ሀብትና ክብር ባገኘ ጊዜ፣ ከአክዓብ ጋር በጋብቻ ተሳሰረ። 2ከጥቂት ዓመታት በኋላም አክዓብን ሊጐበኝ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ብዙ በግና በሬ ዐረደ፤ ከዚያም በሬማት ዘገለዓድ ላይ አደጋ እንዲጥል አግባባው። 3የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት አብረኸኝ ትሄዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱ አብረናችሁ እንሰለፋለን” ሲል መለሰለት። 4ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “አስቀድመህ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቅ” አለው።5ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት ልሂድን ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ሂድ” ብለው መለሱለት።
6ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።
7የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ ደግ ትንቢት ስለማይናገር እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚካያ ነው” ሲል መለሰ።
ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሥ እንዲህ ማለት አይገባውም” አለው።
8የእስራኤልም ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ “ሂድና የይምላን ልጅ ሚካያን በፍጥነት አምጣው” አለው።
9የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር መግቢያ አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 10የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ።
11ሌሎቹ ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በሬማት ገለዓድ ላይ አደጋ ጣልባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
12ሚካያን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ እየተነበዩ ነው፤ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውን ተናገር” አለው።
13ሚካያ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን ብቻ እናገራለሁ” አለ።
14እዚያ በደረሰም ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚካያ ሆይ፤ ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት እንሂድ ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም መልሶ፣ “ሂዱና ድል አድርጉ፤ በእጃችሁ ዐልፈው ይሰጣሉና” አለው።
15ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው።
16ከዚያም ሚካያ፣ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሏል” ሲል መለሰ።
17የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ ደግ ትንቢት እንደማይናገር አልነገርሁህምን?” አለው። 18ሚካያም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 19እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በሬማት ገለዓድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ።
“አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ። 20በመጨረሻም አንድ መንፈስ ወደ ፊት ወጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ።
“እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።
21“እርሱም፣ ‘እሄድና በነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።
“እግዚአብሔርም፣ ‘እንግዲያውስ ሂደህ አሳስተው፤ ይሳካልሃልም’ አለው።
22“አሁንም እነሆ፣ እግዚአብሔር በእነዚህ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት አዝዞብሃል”።
23ከዚያም የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚካያን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ አንተን ያነጋገረህ፣ በየት በኩል ዐልፎኝ ነው?” አለው።
24ሚካያም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።
25ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚካያን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ ላኩት፤ 26እነርሱንም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደኅና እስክመለስም ድረስ ከደረቅ ቂጣና ከውሃ በስተቀር ምንም አትስጡት ብሏል’ በሏቸው።”
27ሚካያም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።
አክዓብ በሬማት ገለዓድ ተገደለ
18፥28-34 ተጓ ምብ – 1ነገ 22፥29-36 28ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ገለዓድ ወጡ። 29የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ።30በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዘዛቸው። 31የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላክም ከእርሱ መለሳቸው፤ 32የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተረዱ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።
33ይሁን እንጂ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው፣ በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል ዐልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው። 34ጦርነቱ ቀኑን ሙሉ እንደ ተፋፋመ ዋለ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ እስከ ምሽት ድረስ ተደግፎ ነበር፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ሞተ።
Copyright information for
AmhNASV