2 Chronicles 24
ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን ማደሱ
24፥1-14 ተጓ ምብ – 2ነገ 12፥1-16 24፥23-27 ተጓ ምብ – 2ነገ 12፥17-21 1ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አርባ ዓመት ገዛ። እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 2ካህኑ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ። 3ዮዳሄ ሁለት ሚስቶች መረጠለት፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለደ።4ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ወሰነ። 5ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦም፣ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በየዓመቱ ለማደስ ገንዘብ ከእስራኤል ሁሉ ሰብስቡ፤ ይህንም አሁኑኑ አድርጉት” አላቸው። ሌዋውያኑ ግን ቸል አሉ።
6ስለዚህ ንጉሡ ሊቀ ካህኑን ዮዳሄን ጠርቶ፣ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴና የእስራኤል ጉባኤ ለምስክሩ ድንኳን እንዲወጣ የወሰኑትን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላተጋሃቸው ለምንድን ነው?” አለው።
7በዚህ ጊዜ የዚያች ክፉ የጎቶልያ ልጆች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሰብረው በመግባት የተቀደሱ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ለበኣል ጣዖታት አገልግሎት እንዲውሉ አድርገው ነበር።
8በንጉሡም ትእዛዝ የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በር አጠገብ በውጭ በኩል አኖሩት። 9ከዚህ በኋላ እስራኤል በምድረ በዳ ሳሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ። 10ሹማምቱ ሁሉ፣ ሕዝቡም ሁሉ ግብሩን በደስታ አመጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጨመሩ። 11ሣጥኑ በሌዋውያኑ እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በሚደርስበት ጊዜ፣ እነርሱም በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም ይመጡና ሣጥኑን አጋብተው ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። ይህን በየቀኑ በማድረግ እጅግ ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ። 12ንጉሡና ዮዳሄም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን አስረከቧቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ድንጋይ ጠራቢዎችንና ዐናጢዎችን እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመጠገን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ቀጠሩ።
13በሥራው ላይ የተሰማሩት ሰዎች ትጉሃን ስለ ነበሩ፣ ሥራው በእጃቸው ተከናወነ፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀደም ሲል በነበረው ዐይነት ዐደሱት፤ አጠናከሩትም። 14ከጨረሱም በኋላ ቀሪውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ዮዳሄ አመጡ፤ በገንዘቡም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ማለትም ለአገልግሎትና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚውሉ ዕቃዎች እንደዚሁም ጭልፋዎችና ሌሎች የወርቅና የብር ዕቃዎችም ተሠሩ። ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘወትር ይቀርብ ነበር።
15ዮዳሄ ሸምግሎ ዕድሜ ከጠገበ በኋላ፣ በመቶ ሠላሳ ዓመቱ ሞተ። 16እርሱም በእስራኤል ውስጥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ መልካም ሠርቷልና በዳዊት ከተማ በነገሥታቱ መቃብር ተቀበረ።
የኢዮአስ ክፋት
17ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ ሹማምት መጥተው ለንጉሡ ታማኝነታቸውን ገለጡ፤ ንጉሡም አደመጣቸው። 18እነርሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ትተው፣ የአሼራን ዐምዶችና ጣዖታትን አመለኩ፤ በበደላቸውም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። 19ወደ እግዚአብሔር ይመልሷቸው ዘንድ እርሱ ነቢያቱን ወደ ሕዝቡ ሰደደ፤ ነቢያቱም መሰከሩባቸው፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም።20የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም፤ እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቷችኋል” አላቸው።
21እነርሱ ግን አሤሩበት፤ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ በድንጋይ ወግረው ገደሉት።
22ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ በዚህ ፈንታ ልጁን ገደለው፤ በሚሞትበትም ጊዜ፣ “እግዚአብሔር ይየው፤ እርሱው ይበቀልህ” አለ።
23በዓመቱም መጨረሻ ▼
▼ምናልባት መስከረም፣ ጥቅምትና ኅዳር
፣ የሶርያ ሰራዊት በኢዮአስ ላይ ዘመተ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምንም ወርሮ የሕዝቡን መሪዎች ሁሉ ደመሰሰ፤ ምርኮውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላከ። 24የሶርያ ሰራዊት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር በጣም የሚበልጠውን ሰራዊት በእጃቸው አሳልፎ ሰጠ፤ ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ በኢዮአስ ላይ ተፈረደበት። 25ሶርያውያንም በወጡ ጊዜ ኢዮአስን ክፉኛ አቍስለው፣ ጥለውት ሄዱ፤ የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ስለ ገደለም፣ ሹማምቱ አሢረውበት በዐልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት። በዚህ ሁኔታም ሞቶ በዳዊት ከተማ ተቀበረ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልተቀበረም። 26በእርሱ ላይ ያሤሩትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቱ የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። 27የወንዶች ልጆቹ ታሪክ፣ ስለ እርሱ የተነገሩት ብዙ ትንቢቶችና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መታደስ በነገሥታቱ የታሪክ መዛግብት ተጽፈዋል። ልጁ አሜስያስም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
Copyright information for
AmhNASV