2 Chronicles 25
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ
25፥1-4 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥1-6 25፥11-12 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥7 25፥17-28 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥8-20 1አሜስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ አልነበረም። 3መንግሥቱን ካጸና በኋላ፣ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ሹማምት በሞት ቀጣቸው። 4እግዚአብሔር በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው ሕግ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው አይገደሉ፤ ልጆችም ስለ ወላጆቻቸው አይገደሉ” a ብሎ ባዘዘው መሠረት አደረገ እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም።5አሜስያስ የይሁዳን ሕዝብ በአንድነት ሰብስቦ፣ እንደየቤተ ሰቡ በሻለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል በመላው ይሁዳና በብንያም መደባቸው። ከዚያም ዕድሜያቸው ሃያና ከሃያ በላይ የሆናቸውን ሰብስቦ፣ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ ሆነው ጋሻና ጦር መያዝ የሚችሉ ሦስት መቶ ሺሕ ሰዎች አገኘ። 6እንዲሁም በመቶ መክሊት ▼
▼በዚህና በቍጥር 9 ላይ 3.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው።
ጥሬ ብር አንድ መቶ ሺሕ ተዋጊዎች ከእስራኤል ቀጠረ። 7ነገር ግን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤልም ሆነ ከማናቸውም የኤፍሬም ሕዝብ ጋር አይደለምና፣ እነዚህ የእስራኤል ወታደሮች ከአንተ ጋር አይዝመቱ። 8ሄደህ፣ ጦርነቱን በቈራጥነት ብትዋጋም እንኳ፣ የመርዳትና የመጣል ኀይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።”
9አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “ታዲያ ለእነዚህ ለእስራኤል ወታደሮች የከፈልሁት መቶ መክሊት እንዴት ይሁን?” ሲል ጠየቀው የእግዚአብሔርም ሰው፣ “እግዚአብሔር ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት።
10ስለዚህ አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እርሱ የመጡትን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው አሰናበታቸው። እነርሱም በይሁዳ ላይ ክፉኛ ተበሳጭተው ነበርና በታላቅ ቍጣ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ተመለሱ።
11አሜስያስም ኀይሉን በሚገባ አደራጅቶ ሰራዊቱን ወደ ጨው ሸለቆ መራ፤ በዚያም ዐሥር ሺሕ የሴይር ወታደሮችን ገደለ። 12የይሁዳ ሰራዊት ሌሎች ዐሥር ሺሕ ሰዎች ማረኩ፤ ወደ አንድ ዐለት ዐናት ላይም አውጥተው ቍልቍል ለቀቋቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ።
13በዚያኑ ጊዜ አሜስያስ ያሰናበታቸውና በጦርነቱ እንዳይካፈሉ የከለከላቸው ወታደሮች፤ ከሰማርያ እስከ ቤትሖሮን ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ ሦስት ሺሕ ሰው ገደሉ፤ እጅግ ብዙ ምርኮም ወሰዱ።
14አሜስያስም ኤዶማያውያንን ደምስሶ በተመለሰ ጊዜ፣ የሴይርን ሕዝብ አማልክት ይዞ መጣ፤ ለራሱም አማልክት አድርጎ በማቆም ሰገደላቸው፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው። 15የእግዚአብሔርም ቍጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይንም ላከበት፤ ነቢዩም፣ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ ማዳን ያልቻሉትን የአሕዛብን አማልክት ርዳታ የጠየቅኸው ለምንድን ነው?” አለው።
16እርሱም በመናገር ላይ ሳለ፣ ንጉሡ፣ “ለመሆኑ አንተን የንጉሥ አማካሪ አድርገን ሾመነሃልን? ዝም አትልም እንዴ! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው።
ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም፣ “ይህን አድርገሃልና ምክሬንም አልሰማህምና፤ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንደ ወሰነ ዐውቃለሁ” አለ።
17የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ አማካሪዎቹን ካማከረ በኋላ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ኢዮአስ፣ “እስቲ ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል ላከበት።
18የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ ግን፣ ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ‘ሚስት እንድትሆነው ሴት ልጅህን ለልጄ ስጠው’ ሲል ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከበት። ከዚያም የዱር አውሬ ከሊባኖስ ወጥቶ ኵርንችቱን ረገጠው። 19ኤዶምን አሸንፌአለሁ ብለህ ራስህን በትዕቢት ክበኸዋል፤ ኰርተሃልም፤ ግን ዐርፈህ እቤትህ ተቀመጥ! በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ታመጣ ዘንድ ችግር የምትጠራው ስለ ምንድን ነው?”
20የኤዶምን አማልክት ማምለክ በመፈለጋቸው፣ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኗልና፣ አሜስያስ አላዳመጣቸውም። 21ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ አደጋ ጣለ። እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ በይሁዳ ውስጥ ቤትሳሚስ በተባለ ስፍራ ፊት ለፊት ተጋጠሙ። 22ይሁዳ በእስራኤል ክፉኛ ተመታ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደየመኖሪያው ሸሸ። 23የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ከኤፍሬም በር እስከ ማእዘኑ በር ድረስ አንድ መቶ ሰማንያ ሜትር ▼
▼ዕብራይስጡ፣ 80 ሜትር ያህል ነው ይላል፤ አንዳንድ ቅጆች ግን ስድስት መቶ ጫማ ይላሉ።
ያህል ርዝመት ያለውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ። 24እርሱም በዖቤድ ኤዶም ጥበቃ ሥር የነበረውንና በቤተ መቅደሱ የተገኘውን ወርቅ፣ ጥሬ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ ከቤተ መንግሥቱም ንብረትና በመያዣ ከያዛቸው ሰዎች ጭምር ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 25የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 26በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነው ሌላው ተግባር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27አሜስያስ እግዚአብሔርን መከተል ከተወ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ስላመፁበት ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ ነገር ግን የሚከታተሉትን ሰዎች ከኋላው ልከው በዚያው በለኪሶ ገደሉት። 28በፈረስ ተጭኖ ከመጣ በኋላም፣ እንደ አባቶቹ ሁሉ በይሁዳ ከተማ ተቀበረ።
Copyright information for
AmhNASV