2 Chronicles 30
ሕዝቅያስ ፋሲካን ማክበሩ
1ሕዝቅያስ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ፣ ለመላው እስራኤልና ለይሁዳ መልእክት ላከ፤ ለኤፍሬምና ለምናሴም ደብዳቤ ጻፈ። 2ንጉሡ፣ ሹማምቱና መላው የኢየሩሳሌም ጉባኤ የፋሲካውን በዓል በሁለተኛው ወር ለማክበር ተስማሙ። 3በቂ ካህናት ራሳቸውን ስላልቀደሱና ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰቡ፣ በዓሉን በወቅቱ ለማክበር አልቻሉም ነበር። 4ንጉሡና መላው ጉባኤም ዕቅዱ ትክክል ሆኖ አገኙት። 5ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር ሕዝቡ እንዲመጣ፣ ከቤርሳቤህ እስከ ዳን ድረስ ዐዋጅ እንዲነገር ወሰኑ፤ በተጻፈው መሠረት በዓሉ ብዛት ባለው ሕዝብ ተከብሮ አያውቅም ነበርና።6መልእክተኞችም በንጉሡ ትእዛዝ፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤
“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እርሱ ወደ ተረፋችሁት፣ ከአሦር ነገሥታትም እጅ ወዳመለጣችሁት፣ ወደ እናንተ እንዲመለስ እናንተም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። 7እንደምታዩት ሁሉ መሣለቂያ እስኪያደርጋቸው ድረስ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። 8እንደ አባቶቻችሁም ዐንገተ ደንዳኖች አትሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ እርሱ ለዘላለም ወደ ቀደሰውም መቅደስ ኑ። አስፈሪ ቍጣው ከእናንተ እንዲመለስም፣ እግዚአብሔር አምላካችሁን አገልግሉ። 9እናንተ ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና ርኅሩኅ ስለሆነ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁን በማረኳቸው ዘንድ ምሕረትን ያገኛሉ፤ ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ። እናንተ ወደ እርሱ ብትመለሱ፣ እርሱም ፊቱን ከእናንተ አይመልስም።”
10መልእክተኞቹም በኤፍሬምና በምናሴ ምድር ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ በመዘዋወር እስከ ዛብሎን ድረስ ሄዱ፤ ሕዝቡ ግን አንቋሸሻቸው፤ ተሣለቀባቸውም። 11ሆኖም ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ጥቂት ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 12እንዲሁም ንጉሡና ሹማምቱ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ያዘዙትን እንዲፈጽሙ አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ነበር።
13በሁለተኛው ወር የቂጣን በዓል ለማክበር እጅግ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ። 14በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎች ነቃቅለው፣ የዕጣን መሠዊያዎችንም ከስፍራው አንሥተው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣሉ።
15በሁለተኛው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ ዐረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ ዐፍረው ስለ ነበር ራሳቸውን ቀደሱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመጡ። 16ከዚያም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ታዘዘው መደበኛ ቦታቸውን ያዙ። ካህናቱም ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ። 17ከጉባኤው መካከል አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያልቀደሱ ስለ ነበሩ፣ ሌዋውያኑ በሥርዐቱ መሠረት ራሳቸውን ላላነጹትና ጠቦቶቻቸውን ለእግዚአብሔር መቀደስ ላልቻሉት ሁሉ የፋሲካውን በጎች ማረድ ነበረባቸው። 18ምንም እንኳ ከኤፍሬም፣ ከምናሴ፣ ከይሳኮርና ከዛብሎን ከመጡት አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያላነጹ ቢሆንም ከተጻፈው ትእዛዝ ውጭ ፋሲካውን በሉ። ሕዝቅያስ ግን እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ቸሩ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይቅር በላቸው፤ 19ምንም እንኳ በመቅደሱ ሥርዐት መሠረት የነጹ ሆነው ባይገኙም፣ የአባቶቻቸው አምላክ የሆነውን እግዚአብሔር አምላካቸውን ለመፈለግ ልባቸውን የሚያዘጋጁትን ሁሉ ይቅር በላቸው።” 20እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም ፈወሰ።
21ሌዋውያኑና ካህናቱ በእግዚአብሔር የዜማ ዕቃ ታጅበው፣ በየዕለቱ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ ▼
▼ወይም ሌዋውያንና ካህናቱ በእግዚአብሔር የዜማ ዕቃ ታጅበው በየዕለቱ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት እስራኤላውያን የቂጣን በዓል በታላቅ ደስታ ለሰባት ቀን አከበሩ፤ 22ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ በንግግሩ አበረታታ። ሰባቱንም ቀን የተወሰነላቸውን ድርሻ እየበሉና የኅብረት መሥዋዕቱንም ▼
▼በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት ይባላል።
እያቀረቡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 23ጉባኤውም ሁሉ በተከታዩ ሰባት ቀን በዓሉን እንደ ገና ለማክበር ተስማሙ፣ ስለዚህ በዓሉን ለሰባት ተጨማሪ ቀን በታላቅ ደስታ አከበሩ። 24የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ አንድ ሺሕ ወይፈን፣ ሰባት ሺሕ በግና ፍየል ለጉባኤው ሰጠ፤ ሹማምቱም እንደዚሁ አንድ ሺሕ ወይፈን፣ ዐሥር ሺሕ በግና ፍየል ሰጡ። እጅግ ብዙ ካህናትም ራሳቸውን ቀደሱ። 25መላው የይሁዳ ጉባኤ፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ፣ ከእስራኤል የተሰበሰበው ጉባኤ ሁሉ፣ እንዲሁም ከእስራኤል የመጡ መጻተኞችና በይሁዳ የሚኖሩ መጻተኞች ደስ አላቸው። 26ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ጊዜ አንሥቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ በዓል ተደርጎ ስለማያውቅ፣ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ። 27ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ እግዚአብሔርም ሰማቸው፤ ጸሎታቸውም ወደ ሰማይ ወደ ቅዱሱ ማደሪያው ደረሰ።
Copyright information for
AmhNASV