የሐዋርያው ዮሐንስ መልእክት – ሁለተኛ

‏ 2 John

1ሽማግሌው፤

በእውነት ለምወድዳት፣ እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወድዷት ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ፤
2በውስጣችን ከሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ከሚሆን እውነት የተነሣ፤

3ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናል።

4ከልጆችሽ አንዳንዶቹ ከአብ በተሰጠን ትእዛዝ መሠረት በእውነት ጸንተው እየሄዱ በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። 5አሁንም እመቤት ሆይ፤ ከመጀመሪያ የነበረችውን እንጂ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍልሽም፤ ይኸውም እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ ነው። 6ይህም ፍቅር፣ በትእዛዞቹ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው። ትእዛዙም ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት በፍቅር እንድትኖሩ ነው።

7ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል። እንዲህ ያለ ማንኛውም ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 8እናንተም የደከማችሁበትን ዋጋ እንዳታጡ፣ ነገር ግን ሙሉ ሽልማት እንድትቀበሉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 9በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ ሁሉ አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን አብም ወልድም አለው። 10ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ፣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምም አትበሉት፤ 11የሚቀበለው ሰው፣ የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና።

12የምጽፍላችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በወረቀትና በቀለም እንዲሆን አልፈልግም፤ ዳሩ ግን ደስታችን ፍጹም ይሆን ዘንድ ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት ላነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

13የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።

Copyright information for AmhNASV