2 Kings 3
ሞዓብ ዐመፀ
1የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ የአክአብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ገዛ። 2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ ክፉ ድርጊቱ ግን አባትና እናቱ እንደ ፈጸሙት ዐይነት አልነበረም፤ አባቱ ያሠራውንም የበኣልን ሐውልት አስወገደ። 3ነገር ግን የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ባሳተበት ኀጢአት ተያዘ፤ ከዚያም አልተላቀቀም።4በዚህ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ ሞሳ በግ ያረባ ነበር፤ እርሱም መቶ ሺሕ ጠቦትና የመቶ ሺሕ አውራ በግ ጠጕር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር። 5አክዓብ ከሞተ በኋላ ግን የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ። 6ስለዚህ በዚያኑ ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ከሰማርያ ተነሥቶ በመሄድ እስራኤልን ሁሉ አሰባሰበ። 7ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “የሞዓብ ንጉሥ ስለ ዐመፀብኝ አብረኸኝ ትዘምታለህን?” ሲል መልእክት ላከበት።
እርሱም፣ “አዎን አብሬህ እዘምታለሁ፤ እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፤ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” በማለት መለሰለት።
8ኢዮሣፍጥም፣ “የምንዘምተው በየትኛው መንገድ ነው” ብሎ ጠየቀው፤
ኢዮራምም “በኤዶም ምድረ በዳ ዐልፈን ነው” ሲል መለሰለት።
9ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከይሁዳ ንጉሥና ከኤዶም ንጉሥ ጋር ለመዝመት ተነሣ። ሰባት ቀን ከዞሩም በኋላ ለሰራዊቱም ሆነ ለእንስሶቻቸው የተረፈ ውሃ አልነበረም።
10የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ወዮ! እግዚአብሔር እኛን ሦስት ነገሥታት የጠራን ለሞዓብ አሳልፎ ሊሰጠን ነውን?” አለ።
11ኢዮሣፍጥ ግን፣ “በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን ለመጠየቅ እንድንችል፣ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” በማለት ጠየቀ።
ከእስራኤል ንጉሥ የጦር አለቆችም አንዱ፣ “ቀድሞ የኤልያስን እጅ ያስታጥብ የነበረው፤ ▼
▼የኤልያስ አገልጋይ ነው።
የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ በዚህ አለ” ብሎ መለሰለት።12ኢዮሣፍጥም፣ “የእግዚአብሔር ቃል ከእርሱ ዘንድ ይገኛል” አለ፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ፣ ኢዮሣፍጥና የኤዶም ንጉሥ አብረው ወደ እርሱ ወረዱ።
13ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ፤ “ከአንተ ጋር ምን የሚያገናኘን ጕዳይ አለና መጣህ፤ አሁን የአባትህና የእናትህ ነቢያት ወዳሉበት ሂድ” አለው።
የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፣ “ይህማ አይሆንም፤ በሞዓብ እጅ አሳልፎ ሊሰጠን እኛን ሦስት ነገሥታት አንድ ላይ የጠራን እግዚአብሔር ነው” አለ።
14ኤልሳዕም እንዲህ አለው፤ “የማገለግለው ሕያው እግዚአብሔርን፣ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባላከብር ኖሮ፣ አንተን አላይም ወይም ጕዳዬ አልልህም ነበር። 15አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ።”
ታዲያ ባለ በገናው በሚደረድርበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔር እጅ በኤልሳዕ ላይ መጣ፤ 16እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር የሚለው እንዲህ ነው፤ ‘በዚህ ሸለቆ ብዙ ጕድጓዶች ቈፍሩ።’ 17እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ነፋስም ሆነ ዝናብ አታዩም፤ ሸለቆው ግን በውሃ ይሞላል፤ እናንተ፣ የቀንድ ከብቶቻችሁና ሌሎች እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ።’ 18ይህ በእግዚአብሔር ፊት ቀላል ነገር ነው። ሞዓብንም በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል።
19“የተመሸጉትን ከተሞችና ያማሩትን ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል ታደርጋላችሁ። ውብ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን በሙሉ ትደፍናላችሁ፤ መልካሙንም ዕርሻ በድንጋይ ታበላሹታላችሁ።”
20በማግስቱም መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ እነሆ፤ ከኤዶም በኩል ውሃ እየጐረፈ መጣ፤ ምድሪቱም ውሃ በውሃ ሆነች።
21በዚህ ጊዜ ነገሥታቱ ሊወጓቸው መምጣታቸውን ሞዓባውያን ሁሉ ሰምተው ነበርና፣ ልጅም ሆነ ሽማግሌ፣ መሣሪያ መያዝ የቻለ ሁሉ ተጠርቶ በመውጣት በጠረፉ ላይ ይጠባበቅ ጀመር። 22በማግስቱም ጧት ማልደው ሲነሡም፣ ፀሓይ በውሃው ላይ ታንጸባርቅ ነበር። ማዶ ላሉት ሞዓባውያንም፣ ውሃው እንደ ደም ቀልቶ ታያቸው። 23ስለዚህ፣ “ያ እኮ ደም ነው! ያለ ጥርጥር ነገሥታቱ እርስ በርስ ተዋግተው ተራርደዋል። እንግዲህ ሞዓብ ወደ ምርኮህ ዙር!” ተባባሉ።
24ሞዓባውያን ወደ እስራኤል ሰፈር ሲወጡም፣ እስራኤላውያን ተነሥተው ወጓቸው፤ ሞዓባውያንም ከፊታቸው ሸሹ። ከዚያም እስራኤላውያን ምድሪቱን ወርረው ሞዓባውያንን ፈጇቸው። 25ከተሞቹን ደመሰሱ፤ መልካሙን የዕርሻ መሬት ሁሉ እስኪሸፍነው ድረስ፣ እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ድንጋይ ጣለበት፤ ምንጮቹን በሙሉ ደፈኑ፤ ጥሩ ጥሩውንም ዛፍ ሁሉ ቈርጠው ጣሉ። ቂርሐራሴት ብቻ ከነድንጋይዋ ቀርታ ነበር፤ እርሷንም ቢሆን ባለ ወንጭፉ ሰራዊት ከብቦ አደጋ ጣለባት።
26የሞዓባውያን ንጉሥ በጦርነቱ መሸነፉን እንዳወቀ፣ ሰይፍ የታጠቁ ሰባት መቶ ሰዎች ይዞ የኤዶም ንጉሥ ወዳለበት ጥሶ ለመግባት ሞከረ፤ ነገር ግን አልተሳካላቸውም። 27ከዚያም በእግሩ ተተክቶ የሚነግሠውን፣ የበኵር ልጁን ወስዶ በከተማዪቱ ቅጥር ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው። በእስራኤልም ላይ ታላቅ ቍጣ ሆነ፤ ከዚያም ለቅቀው ወደ ገዛ ምድራቸው ተመለሱ።
Copyright information for
AmhNASV