2 Peter 2
ሐሰተኛ መምህራንና መጨረሻቸው
1ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡ መካከል እንደ ነበሩ፣ እንዲሁም በእናንተ መካከል ሐሰተኞች መምህራን ይነሣሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው፣ ጥፋት የሚያስከትል የስሕተት ትምህርት በስውር ያስገባሉ፤ በዚህም በራሳቸው ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣሉ። 2ብዙዎች አስነዋሪ ድርጊቶቻቸውን ይከተላሉ፤ በእነርሱም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል። 3እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን እየተስገበገቡ በፈጠራ ታሪካቸው ይበዘብዟችኋል። ፍርዳቸው ከጥንት ጀምሮ ዝግጁ ነው፤ መጥፊያቸውም አያንቀላፋም።4እግዚአብሔር ኀጢአት የሠሩትን መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ▼
▼በግሪኩ ታርታሩስ ይለዋል።
ከጣላቸውና በጨለማ ጕድጓድ ውስጥ ለፍርድ ካስቀመጣቸው፣ 5የጽድቅ ሰባኪ የነበረውንም ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ፣ ለቀድሞው ዓለም ሳይራራ በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ ካመጣ፣ 6ደግሞም ኀጢአት ለሚያደርጉ ሁሉ ምሳሌ እንዲሆኑ፣ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ዐመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ ከፈረደባቸው፣ 7ጻድቅ የሆነውንና በዐመፀኞች ሴሰኛ ድርጊት እየተሣቀቀ የኖረውን ሎጥን ካዳነ፣ 8ያ ጻድቅ ሰው በእነርሱ መካከል ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው ነገር ነፍሱ ዕለት ዕለት በዐመፀኛ ድርጊታቸው ብትጨነቅም፣ 9ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ▼▼ወይም ዐመፀኞችን ለቅጣት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ
ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል። 10በተለይም በርኩስ ምኞት የሥጋ ፍላጎታቸውን ▼▼ወይም የኀጢአተኛ ባሕርያቸውን
የሚከተሉትንና ሥልጣንን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል።እነዚህ ሰዎች ደፋሮችና እብሪተኞች ስለሆኑ ሰማያውያንን ፍጡራን ሲሳደቡ አይፈሩም፤ 11ነገር ግን መላእክት ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ኀያል ሆነው ሳሉ፣ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብ ቃል አይሰነዝሩም። 12እነዚህ ሰዎች ግን ምንም በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ፤ እነርሱም ለመያዝና ለመገደል እንደ ተወለዱ፣ በስሜታቸው ብቻ እንደሚመሩና ልቦናም እንደሌላቸው አራዊት ናቸው፤ የሚጠፉትም እንደ እንስሳት ነው።
13ለዐመፃቸው የሚገባውን የዐመፅ ዋጋ ይቀበላሉ። በጠራራ ፀሓይ ሲፈነጥዙ እንደ ደስታ ይቈጥሩታል፤ በግብዣ ላይ ሳሉ ነውረኞችና ርኩሶች ሆነው ከእናንተም ጋር በፍቅር ግብዣ ላይ ▼
▼በአንዳንድ ቅጆች በፍቅር ግብዣቸው ላይ የሚል የለም።
ይቀመጣሉ። 14ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት ያስታሉ፤ ሥሥትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው! 15ቀናውን መንገድ ትተው፣ የዐመፅን ደመወዝ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ስተዋል፤ 16እርሱ ግን ስለ መተላለፉ ተገሥጿል፤ መናገር የማይችል አህያ በሰው ቋንቋ ተናግሮ የነቢዩን እብደት ገታ። 17እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በዐውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ የሚጠብቃቸውም ድቅድቅ ጨለማ ነው፤ 18ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች በሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና። 19እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው ሳሉ፣ ሌሎችን ነጻ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተገዛለት ለዚያ ነገር ባሪያ ነውና። 20ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ እንደ ገና ተጠላልፈው ቢሸነፉ፣ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ ይሆንባቸዋል። 21የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ፣ ቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት ይሻላቸው ነበር። 22“ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል” እንዲሁም “ዐሣማ ቢታጠብም ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል” የሚለው ምሳሌ እውን ይሆንባቸዋል።
Copyright information for
AmhNASV