2 Samuel 9
ዳዊትና ሜምፊቦስቴ
1ዳዊትም፣ “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖር ይሆን?” በማለት ጠየቀ።2በዚያን ጊዜ ከሳኦል ቤት ሲባ የሚባል አንድ አገልጋይ ስለ ነበር፣ ወደ ዳዊት እንዲሄድ ነገሩት። ንጉሡም፣ “ሲባ የምትባለው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም፣ “አዎን እኔ አገልጋይህ ነኝ” አለ።
3ንጉሡም፣ “የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው የለምን?” ሲል ጠየቀው።
ሲባም ለንጉሡ፣ “እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” ብሎ መለሰለት።
4ንጉሡም፣ “የት ነው ያለው?” ብሎ ጠየቀ።
ሲባም፣ “ሎደባር በተባለ ስፍራ በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ብሎ መለሰለት።
5ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት፣ ሜምፊቦስቴን ከዓሚኤል ከማኪር ቤት ከሎደባር ልኮ አስመጣው።
6የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት በመጣ ጊዜ፣ አክብሮቱን ለመግለጥ ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።
ዳዊትም፣ “ሜምፊቦስቴ” ብሎ ጠራው።
እርሱም፣ “እነሆ፤ አገልጋይህ” አለ።
7ዳዊትም፣ “አትፍራ፤ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል በርግጥ ቸርነት አደርግልሃለሁና። የአባትህን የሳኦልን ምድር በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም ከማዕዴ ትበላለህ” አለው።
8ሜምፊቦስቴ ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፣ “እንደ ሞተ ውሻ ለምቈጠር ለእኔ ይህን ያህል የምታደርግልኝ አገልጋይህ ኧረ ማን ነኝ?” አለ።
9ከዚያም ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ሲባን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “የሳኦልና የቤተ ሰቡ የሆነውን ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቼዋለሁ። 10አንተ፣ ልጆችህና አገልጋዮችህ የጌታችሁ የልጅ ልጅ የሚበላውን እንዲያገኝ መሬቱን ዕረሱለት፣ ምርቱንም አግቡለት። የጌታህ የልጅ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ምንጊዜም ከማእዴ ይበላል።” በዚያን ጊዜ ሲባ ዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆችና ሃያ አገልጋዮች ነበሩት።
11ከዚያም ሲባ ንጉሡን፣ “ጌታዬ ንጉሥ፣ አገልጋዩን ያዘዘውን ሁሉ፣ አገልጋይህም ይፈጽመዋል” አለው። ስለዚህም ሜምፊቦስቴ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ሆኖ ከዳዊት ▼
▼የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ከእኔ ይላል።
ማእድ ይበላ ነበር። 12ሜምፊቦስቴ ሚካ የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ ነበረው፤ የሲባ ቤተ ሰዎች በሙሉ ሜምፊቦስቴን ያገለግሉት ነበር። 13ሜምፊቦስቴም ሁልጊዜ ከንጉሥ ማእድ ስለሚበላ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነው፤ ሁለት እግሮቹም ሽባ ነበሩ።
Copyright information for
AmhNASV