‏ 2 Timothy 2

1እንግዲህ ልጄ ሆይ፤ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። 2በብዙ ምስክር ፊት ከእኔ የሰማኸውን፣ ሌሎችን ለማስተማር ብቃት ላላቸው ለታመኑ ሰዎች ዐደራ ስጥ። 3እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር ከእኛ ጋር መከራን ተቀበል። 4በውትድርና የሚያገለግል ሰው አዛዡን ለማስደሰት ይጥራል እንጂ በሌላ ሥራ ራሱን አያጠላልፍም። 5እንደዚሁም በውድድር የሚሳተፍ ሰው፣ የውድድሩን ሕግ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም። 6ትጉህ ገበሬም ከሰብሉ ለመጠቀም የመጀመሪያው ሊሆን ይገባዋል። 7እኔ የምለውን ልብ በል፤ ጌታ በሁሉም ነገር ማስተዋልን ይሰጥሃልና።

8ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ዐስብ፤ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው፤ 9ለዚህም እንደ ወንጀለኛ እስከ መታሰር ድረስ መከራን እየተቀበልሁ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። 10ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እነርሱም ያገኙ ዘንድ፣ ለተመረጡት ስል ሁሉንም በመታገሥ እጸናለሁ።

11እንዲህ የሚለው ቃል የታመነ ነው፤

ከእርሱ ጋር ከሞትን፣
ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን።
12ብንጸና፣
ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን።
ብንክደው፣
እርሱ ደግሞ ይክደናል፤
13ታማኞች ሆነን ባንገኝ፣
እርሱ ታማኝ እንደ ሆነ ይኖራል፤
ራሱን መካድ አይችልምና።

እግዚአብሔር የተቀበለው ሠራተኛ

14ስለ እነዚህ ነገሮች ማሳሰብህን አትተው፤ በቃላት እንዳይነታረኩ በእግዚአብሔር ፊት አስጠንቅቃቸው፤ ይህ ጥቅም የሌለው፣ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። 15እንደማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ የተመሰከረለት ሠራተኛ፣ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ልታቀርብ ትጋ። 16እግዚአብሔርን ከማያስከብር ከንቱ ልፍለፋ ራቅ፤ በዚህ ነገር የተጠመዱ ሰዎች ከእግዚአብሔር እየራቁ ይሄዳሉና። 17ትምህርታቸው እንደማይሽር ቍስል ይሠራጫል፤ ከእነዚህም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኛሉ፤ 18እነዚህም ከእውነት ርቀው የሚባዝኑ ናቸው። እነርሱም ትንሣኤ ሙታን ከዚህ በፊት ሆኗል እያሉ የአንዳንዶቹን እምነት ይገለብጣሉ። 19ይሁን እንጂ፣ “ጌታ የእርሱ የሆኑትን ያውቃል” ደግሞም፣ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሟል።

20በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ ሳይሆን፣ የዕንጨትና የሸክላ ዕቃም ይኖራል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ለከበረ፣ ሌሎቹም ላልከበረ አገልግሎት ይውላሉ። 21እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ከጠቀስኋቸው ነገሮች ቢያነጻ፣ ለክቡር አገልግሎት የሚውል፣ የተቀደሰ፣ ለጌታው የሚጠቅም፣ ለመልካም ሥራም ሁሉ የተሰናዳ ዕቃ ይሆናል።

22ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋርም ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ተከታተል። 23ከማይረባና ትርጕም የለሽ ከሆነ ክርክር ራቅ፤ ምክንያቱም እነዚህ ጠብን እንደሚያስከትሉ ታውቃለህ። 24የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቃት ያለው፣ ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል፤ 25እውነትን ወደ ማወቅ ይደርሱ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን እንደሚሰጣቸው ተስፋ በማድረግ የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚያቃና መሆን ይኖርበታል፤ 26ይኸውም ወደ አእምሯቸው ይመለሳሉ፤ ፈቃዱን ሊያስፈጽማቸው ምርኮኛ አድርጎ ከያዛቸው ከዲያብሎስ ወጥመድም ያመልጣሉ በማለት ነው።

Copyright information for AmhNASV