Acts 22
1“ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አሁን የማቀርብላችሁን የመከላከያ መልሴን ስሙኝ።” 2እነርሱም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ፣ ከፊት ይልቅ ጸጥ አሉ።ጳውሎስም እንዲህ አለ፤ 3“እኔ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ የተወለድሁ አይሁዳዊ ስሆን፣ ያደግሁት ግን በዚህ ከተማ ነው። የአባቶቻችንን ሕግ በገማልያል እግር ሥር ተቀምጬ በሚገባ ተምሬአለሁ፤ ዛሬ እናንተ እንዲህ የምትቀኑለትን ያህል እኔም ለእግዚአብሔር እቀና ነበር። 4ይህን መንገድ የሚከተሉትንም እስከ ሞት ድረስ እያሳደድሁ፣ ወንዶችንም ሴቶችንም አስሬ ወደ ወህኒ እጥላቸው ነበር። 5ይህን ተግባሬን ሊቀ ካህናቱም ሆነ ሸንጎው ሁሉ ሊመሰክሩ ይችላሉ። ከእነርሱ ደብዳቤ ተቀብዬ ደማስቆ ወዳሉት ወንድሞቻቸው በመሄድ፣ እነዚህን ሰዎች አሳስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥቼ ለማስቀጣት ወደዚያ እሄድ ነበር።
6“ስንጓዝም እኩለ ቀን ገደማ ወደ ደማስቆ እንደ ተቃረብሁ፣ ድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ በራ፤ 7እኔም ምድር ላይ ወደቅሁ፤ ከዚያም፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።
8“እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ አልሁት።
“እርሱም፣ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ። 9ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አዩ፤ ነገር ግን የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ በትክክል አልሰሙም።
10“እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ምን ላድርግ?’ አልሁት።
“ጌታም፣ ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ሁሉ ይነግሩሃል’ አለኝ። 11ከብርሃኑም ጸዳል የተነሣ ዐይኔ ስለ ታወረ፣ ከእኔ ጋር የነበሩት እጄን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አደረሱኝ።
12“ከዚያም ሐናንያ የተባለ ሰው ሊያየኝ ወደ እኔ መጣ፤ እርሱም ሕግን በጥንቃቄ የሚጠብቅና በዚያ በሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ነበረ። 13በአጠገቤም ቆሞ፣ ‘ወንድም ሳውል ሆይ፤ ዐይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ፤ እኔም በዚያችው ቅጽበት አየሁት።
14“እርሱም ቀጥሎ እንዲህ አለ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና ቃሉን ከአንደበቱ እንድትሰማ መርጦሃል፤ 15ስላየኸውና ስለ ሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆነዋለህና። 16ታዲያ፣ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነሥተህ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’
17“ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ በቤተ መቅደስ ስጸልይም ተመሰጥሁ፤ 18ጌታም ሲናገረኝ አየሁ፤ እርሱም አሁኑኑ፣ ‘ፈጥነህ ከኢየሩሳሌም ውጣ! ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና’ አለኝ።
19“እኔም እንዲህ አልሁት፤ ‘ጌታ ሆይ፤ በአንተ የሚያምኑትን ሰዎች ለማሰርና ለመደብደብ፣ በየምኵራቡ ስዞር እንደ ነበር እነዚህ ሰዎች ያውቃሉ፤ 20ደግሞም የአንተን ሰማዕት ▼
▼ወይም ምስክር
የእስጢፋኖስን ደም በሚያፈስሱበት ጊዜ፣ በድርጊታቸው ተስማምቼ በቦታው ቆሜ የገዳዮቹን ልብስ እጠብቅ ነበር።’ 21“ጌታም፣ ‘ሂድ፤ በሩቅ ወዳሉት አሕዛብ እልክሃለሁና’ አለኝ።”
ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑ ታወቀ
22ሕዝቡም ይህን ቃል እስኪናገር ድረስ ሰሙት፤ ከዚህ በኋላ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ፣ “ይህስ ከምድር ገጽ ይወገድ! በሕይወት መኖር አይገባውም!” ብለው ጮኹበት።23እነርሱም እየጮኹና ልብሳቸውን እየወረወሩ፣ ትቢያም ወደ ላይ እየበተኑ ሳሉ፣ 24የጦር አዛዡ ጳውሎስን ወደ ጦር ሰፈር እንዲያስገቡትና ሕዝቡ ለምን እንዲህ እንደሚጮኹበት እየተገረፈ እንዲመረመር ትእዛዝ ሰጠ። 25ጳውሎስም በጠፍር ወጥረው ሊገርፉት ሲሉ፣ አጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ፣ “አንድን የሮም ዜጋ ያለ ፍርድ ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋልን?” አለው።
26የመቶ አለቃውም ይህን ሲሰማ፣ ወደ ጦር አዛዡ ቀርቦ፣ “ምን እያደረግህ እንደ ሆነ ዐውቀሃል? ሰውየው እኮ ሮማዊ ነው” አለው።
27አዛዡም ወደ ጳውሎስ ቀርቦ፣ “አንተ ሰው እስቲ ንገረኝ፤ ሮማዊ ነህን?” አለው።
እርሱም፣ “አዎን፤ ነኝ” አለው።
28አዛዡም መልሶ፣ “እኔ ይህን ዜግነት ያገኘሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” አለ።
ጳውሎስም፣ “እኔ ግን ከተወለድሁ ጀምሮ ሮማዊ ነኝ” አለው።
29ስለዚህ እነዚያ ሊመረምሩት ያሰቡት ሰዎች ወዲያው ከእርሱ ሸሹ፤ የጦር አዛዡም የሮም ዜጋ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ በሰንሰለት አስሮት ስለ ነበር ፈራ።
ጳውሎስ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቀረበ
30በማግስቱም የጦር አዛዡ፣ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበት ትክክለኛው ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ስለ ፈለገ ፈታው፤ ከዚያም የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባላት በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።
Copyright information for
AmhNASV