Deuteronomy 23
ከእግዚአብሔር ጉባኤ መለየት
1ብልቱ የተቀጠቀጠ ወይም የተቈረጠ ማናቸውም ሰው ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።2ዲቃላም ይሁን የዲቃላው ዘር የሆነ ሁሉ፣ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እንኳን ቢሆን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ።
3አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወይም ማናቸውም የእርሱ ዘር፣ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ ቢሆን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ አይግባ። 4ምክንያቱም ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በጕዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እህል ውሃ ይዘው አልተቀበሏችሁም፤ በመስጴጦምያ በምትገኘው በፐቶር ▼
▼ይኸውም ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ነው።
ይኖር የነበረውን የቢዖር ልጅ በለዓምን አንተን እንዲረግም በገንዘብ ገዙት። 5ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በለዓምን አልሰማውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስለሚወድህ ርግማኑን በረከት አደረገልህ። 6በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ሰላምን ለእነርሱ አትመኝ። 7ወንድምህ ስለሆነ ኤዶማዊውን አትጸየፈው፤ መጻተኛ ሆነህ በአገሩ ኖረሃልና ግብፃዊውን አትጥላው። 8ለእነርሱ የተወለዱላቸው የሦስተኛው ትውልድ ልጆች ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ መግባት ይችላሉ።
የጦር ሰፈር ንጽሕና አጠባበቅ
9ጠላትህን ለመውጋት ወጥተህ በሰፈርህ ጊዜ፣ ከማናቸውም ርኩሰት ራስህን ጠብቅ። 10ከመካከላችሁ ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር፣ ከሰፈር ወጥቶ እዚያው ይቈይ። 11እየመሸ ሲመጣ ግን ገላውን ይታጠብ፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ወደ ሰፈሩ ይመለስ።12ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ። 13ከትጥቅህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቈፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት። 14አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን።
ልዩ ልዩ ሕጎች
15አንድ ባሪያ ከአሳዳሪው ኰብልሎ ወደ አንተ ቢመጣ፣ ለአሳዳሪው አሳልፈህ አትስጠው። 16ደስ በሚያሰኘው ቦታና ራሱ በመረጠው ከተማ በመካከልህ ይኑር፤ አንተም አታስጨንቀው።17ወንድ ወይም ሴት እስራኤላዊ የቤተ ጣዖት አመንዝራ አይሁን። 18ለዝሙት ዐዳሪ ሴት ወይም ለወንደቃ ▼
▼ዕብራይስጡ፣ ውሻ ይላል።
የተከፈለውን ዋጋ ለማናቸውም ስእለት አድርገህ ለመስጠት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቤት አታምጣ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሁለቱንም ይጸየፋቸዋልና። 19የገንዘብ፣ የእህል ወይም የማንኛውንም ነገር ወለድ ለማግኘት ለወንድምህ በወለድ አታበድር። 20ባዕድ ለሆነ ሰው ወለድ ማበደር ትችላለህ፤ ነገር ግን ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እጅህ በሚነካው በማናቸውም ነገር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲባርክህ ለእስራኤላዊ ወንድምህ በወለድ አታበድረው።
21ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስእለት ከተሳልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አጥብቆ ከአንተ ይሻዋልና፣ ኀጢአት እንዳይሆንብህ ለመክፈል አትዘግይ። 22ሳትሳል ብትቀር ግን በደለኛ አትሆንም። 23በአንደበትህ የተናገርኸውን ሁሉ ለመፈጸም ጠንቃቃ ሁን፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በገዛ አንደበትህ ፈቅደህ ስእለት ተስለሃልና።
24ወደ ባልንጀራህ የወይን ተክል ቦታ በምትገባበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል መብላት ትችላለህ፤ ነገር ግን አንዳችም በዕቃህ አትያዝ። 25ወደ ባልንጀራህ ዕርሻ በምትገባበት ጊዜ፣ እሸት መቅጠፍ ትችላለህ፤ በሰብሉ ላይ ግን ማጭድ አታሳርፍበት።
Copyright information for
AmhNASV