‏ Deuteronomy 4

ሙሴ እስራኤላውያን እንዲታዘዙ ማስጠንቀቁ

1አሁንም እስራኤል ሆይ፤ በሕይወት እንድትኖሩ፣ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ምድር እንድትገቡና እንድትወርሱ የማስተምራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ ጠብቋቸውም። 2ባዘዝኋችሁ ላይ አትጨምሩ፤ ከእርሱም አትቀንሱ፤ ነገር ግን የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ጠብቁ።

3 እግዚአብሔር (ያህዌ) በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቷቸዋል፤ 4አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ።

5ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ (ያህዌ ኤሎሂም) ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ። 6በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና። 7በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? 8ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው?

9ዐይኖቻችሁ ያዩአቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው። 10“በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ። 11ተራራው በጥቍር ደመናና በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ ሳለ ነበልባሉ ሰማይ እስከሚደርስ ድረስ በተቃጠለ ጊዜ መጥታችሁ ከተራራው ግርጌ ቆማችሁ። 12ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳቱ ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ እናንተም የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፤ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅ ብቻ ነበርና። 13እርሱ ኪዳኑን ይኸውም እንድትከተሏቸው ያዘዛችሁን ዐሥርቱን ትእዛዛት ዐወጀላችሁ፤ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፤ 14ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ የምትከተሏቸውን ሥርዐትና ሕግ እንዳስተምራችሁ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዘዘኝ።

ጣዖትን ማምለክ ስለ መከልከሉ

15 እግዚአብሔር (ያህዌ) በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ውስጥ በተናገራችሁ ቀን ምንም ዐይነት መልክ ከቶ አላያችሁም፤ ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ 16ይኸውም እንዳትረክሱ፣ በወንድ ወይም በሴት መልክ በማናቸውም ዐይነት ምስል የተቀረጸ ጣዖት ለራሳችሁ እንዳታበጁ፣ 17ወይም በምድር ላይ የሚኖር የማናቸውንም እንስሳ ወይም በአየር ላይ የሚበርር የማናቸውንም ወፍ፣ 18ወይም በደረቱ የሚሳብ የማናቸውንም ፍጡር ወይም በውሃ ውስጥ የሚኖር የማናቸውንም ዓሣ ምስል እንዳታደርጉ ነው። 19ወደ ሰማይ ቀና ብለህ ፀሓይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን፣ የሰማይ ሰራዊትንም ሁሉ በምትመለከትበት ጊዜ፣ ወደ እነርሱ እንዳትሳብና እንዳትሰግድላቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከሰማይ በታች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ድርሻ አድርጎ የሰጣቸውንም ነገሮች እንዳታመልክ ተጠንቀቅ። 20እናንተን ግን ልክ ዛሬ እንደ ሆናችሁት ሁሉ ርስቱ ትሆኑለት ዘንድ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እናንተን ከብረት ማቅለጫ ምድጃ፣ ከግብፅ አውጥቶ አመጣችሁ።

21በእናንተም ምክንያት እግዚአብሔር እኔን ተቈጣኝ፤ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገርና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ። 22እኔም በዚህች ምድር እሞታለሁ፤ ዮርዳኖስን አልሻገርም፤ እናንተ ግን ልትሻገሩ ነው፤ ያችንም መልካም ምድር ትወርሳላችሁ። 23አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባውን ኪዳን እንዳትረሱ ተጠንቀቁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የከለከለውን ጣዖት በማናቸውም ዐይነት መልክ ለራሳችሁ አታብጁ። 24አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ (ኤሎሂም) ነውና።

25ልጆችንና የልጅ ልጆችን ከወለዳችሁና በምድሪቱም ላይ ለረዥም ጊዜ ከኖራችሁ በኋላ ራሳችሁን በማርከስ ማንኛውንም ዐይነት ጣዖት ብታበጁ፣ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ክፋት በማድረግ ለቍጣ ብታነሣሡት፣ 26ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትወርሷት ምድር ላይ ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ በዚህ ቀን ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ምስክሮች አድርጌ እጠራለሁ፤ በዚያ ቦታ ብዙ ዘመን አትኖሩም፤ ፈጽሞ ትጠፋላችሁ። 27እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፤ እግዚአብሔር በሚበትናችሁ አሕዛብ መካከል የምትተርፉት ጥቂቶቻችሁ ብቻ ናችሁ። 28እዚያም፣ ማየት ወይም መስማት ወይም መብላት ወይም ማሽተት በማይችሉ በሰው እጅ በተሠሩ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካላችሁ። 29ነገር ግን እዚያም ሆናችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ብትፈልጉት ታገኙታላችሁ። 30ስትጨነቅና ይህ ሁሉ ነገር ሲደርስብህ ያን ጊዜ፣ በኋለኞቹ ዘመናት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትመለሳለህ፤ ትታዘዝለታለህም። 31አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሓሪ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና አይተውህም ወይም አያጠፋህም፤ ወይም ደግሞ ለአባቶችህ በመሐላ ያጸናላቸውን ቃል ኪዳን አይረሳም።

እግዚአብሔር አምላክ ነው

32እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ቀን ጀምሮ እናንተ ከመኖራችሁ በፊት ስለ ነበረው የቀድሞ ዘመን ጠይቁ፤ ከአንዱ የሰማይ ጫፍ እስከ ሌላው የሰማይ ጫፍ ድረስ ጠይቁ፤ እንደዚህ ያለ ታላቅ ነገር ከቶ ተደርጎ ወይስ እንደዚህ ዐይነት ነገር ከቶ ተሰምቶ ያውቃልን? 33ከእሳት ውስጥ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ እንደ እናንተ የሰማና በሕይወት የኖረ ከቶ ሌላ ሕዝብ አለን? 34አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን?

35 እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኑን፣ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታዩ ተደረገ። 36ሊገሥጽህ ድምፁን ከሰማይ እንድትሰማ አደረገ፤ በምድርም ላይ አስፈሪ እሳቱን አሳየህ፤ ከእሳቱም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። 37አባቶችህን ከመውደዱ የተነሣና ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን ስለ መረጠ፣ ከአንተ ጋር በመሆን በታላቅ ኀይሉ ከግብፅ አወጣህ፤ 38ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ከፊትህ በማስወጣት ወደ ምድራቸው አስገብቶህ ለአንተ ርስት አድርጎ ለመስጠት ነው።

39እንግዲህ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኑን ዛሬ ዕወቅ፤ በልብህም ያዘው፤ ሌላም የለም። 40ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለዘላለም በሚሰጥህም ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፣ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ጠብቅ።

የመማፀኛ ከተሞች

4፥41-43 ተጓ ምብ – ዘኍ 35፥6-34፤ ዘዳ 19፥1-14፤ ኢያ 20፥1-9 41በዚያን ጊዜ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ሦስት ከተሞችን ለየ፤ 42ይኸውም የቈየ ጠላትነት ሳይኖር፣ በድንገት ባልንጀራውን የገደለ ማናቸውም ሰው ሸሽቶ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በመሄድ ሕይወቱን ማትረፍ ይችል ዘንድ ነው። 43ከተሞቹም በምድረ በዳው በከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኘው ቦሶር ለሮቤላውያን፣ በገለዓድ የምትገኘው ራሞት ለጋዳውያን፣ በባሳን ያለችው ጎላን ለምናሴያውያን ነበሩ።

ስለ ሕጉ የተሰጠ ማብራሪያ

44ሙሴ በእስራኤላውያን ፊት የደነገገው ሕግ ይህ ነው። 45ከግብፅ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው መመሪያዎች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች እነዚህ ናቸው፤ 46ይህም ከግብፅ በወጡ ጊዜ በሙሴና በእስራኤላውያን ድል በተደረገው፣ በሐሴቦን በነገሠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፣ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በቤተ ፌጎር አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው። 47ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን፣ የእርሱን ምድርና የባሳንን ንጉሥ የዐግን፣ የሁለቱን አሞራውያን ነገሥታት ምድር ርስት አድርገው ወሰዱ። 48ይህም ምድር በአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሴዎን
የዕብራይስጡና የሱርስቱ ትርጕም፣ ሢርዮን ይለዋል (ዘዳ 3፥9 ይመ)
ተራራ ማለትም እስከ አርሞንዔም የሚደርስ ሲሆን፣
49በዮርዳኖስ ምሥራቅ ያለውን ዓረባን በሙሉና ከፈስጋ ተረተር በታች ያለውን የዓረባ ባሕር
ይኸውም የሙት ባሕር ነው።
ያጠቃልላል።

Copyright information for AmhNASV