‏ Deuteronomy 5

ዐሥርቱ ትእዛዛት

5፥6-21 ተጓ ምብ – ዘፀ 20፥1-17 1ሙሴ እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤

እስራኤል ሆይ፤ በዛሬዋ ዕለት በጆሯችሁ የምነግራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ አጥኗቸው፤ በጥንቃቄም ጠብቋቸው።
2አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። 3እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን የገባውም ከአባቶቻችን ጋር ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ በሕይወት ከምንገኘው ከእኛ ከሁላችን ጋር ነው። 4እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ፊት ለፊት አነጋገራችሁ። 5እናንተ ግን እሳቱን በመፍራት ወደ ተራራው ስላልወጣችሁ፣ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ለእናንተ እነግራችሁ ዘንድ እኔ በእግዚአብሔርና (ያህዌ) በእናንተ መካከል ቆምሁ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤

6“ከባርነት ምድር፣ ከግብፅ ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እኔ ነኝ።

7“ከእኔ በቀር
ወይም፣ ከፊቴ ተብሎ መተርጐም ይችላል።
ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።
8በላይ በሰማይ፣ በታች በምድር ላይ ባለው ወይም ከምድር በታች ውሃ ውስጥ በሚኖር በማንኛውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ፤ 9እኔ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ)፣ የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ለእነርሱ አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸው። 10ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ቸርነትንና ፍቅርን እገልጣለሁ።
11 እግዚአብሔር (ያህዌ) ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን ሳይቀጣው አይቀርምና፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስም በከንቱ አታንሣ።
12አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት የሰንበትን ቀን ቀድሰህ አክብረው። 13ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን። 14ሰባተኛው ቀን ግን የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሰንበት ነው። በዚህም ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ በሬህ፣ አህያህ ወይም ማናቸውም እንስሳህ ወይም ደግሞ በደጅህ ያለ እንግዳ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ። ይህም አንተ እንዳረፍህ ሁሉ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ እንዲያርፉ ነው። 15በግብፅ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።
16አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።
17አትግደል።
18አታመንዝር።
19አትስረቅ።
20በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
21የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የእርሱ በሆነው ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”

22 እግዚአብሔር (ያህዌ) በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዞቹ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዞቹንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠኝ።

23ተራራው በእሳት ሲቃጠል፣ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፣ እናንተ የየነገዶቻችሁ አለቆችና ሽማግሌዎቻችሁም በሙሉ ወደ እኔ ዘንድ መጣችሁ፤ 24እንዲህም አላችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ክብሩንና ግርማውን አሳይቶናል፤ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል። እግዚአብሔር አነጋግሮትም እንኳ፣ ሰው በሕይወት ሊኖር እንደሚችል በዛሬው ቀን አይተናል። 25ከእንግዲህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ድምፅ ብንሰማ እንሞታለን፤ ይህችም ታላቅ እሳት ፈጽማ ታጠፋናለች፤ ታዲያ ለምን እንሙት? 26ለመሆኑ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር እኛ እንደ ሰማነው ሁሉ፣ የሕያው እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ ሰምቶ በሕይወት ለመኖር የቻለ ከሥጋ ለባሽ ማን አለ? 27አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚለውን ሁሉ አድምጥ፤ ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚነግርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንሰማለን፤ እናደርገዋለንም።”

28ይህን ስትነግሩኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) አለኝ፤ “ይህ ሕዝብ ምን እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ያሉትም ሁሉ መልካም ነው። 29ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!

30“ሄደህ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ ንገራቸው። 31አንተ ግን እንዲወርሷት በምሰጣቸው ምድር እንዲጠብቋቸው የምታስተምራቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ እንድሰጥህ እዚሁ ከእኔ ዘንድ ቈይ።

32“እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ያዘዛችሁን ለመፈጸም ተጠንቀቁ፤ ቀኝም ግራም አትበሉ። 33በምትወርሷት ምድር በሕይወት ለመኖር እንድትችሉ፣ መልካም እንዲሆንላችሁና ዕድሜያችሁም እንዲረዝም፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።”

Copyright information for AmhNASV