‏ Ecclesiastes 1

ሁሉም ነገር ከንቱ ነው

1በኢየሩሳሌም የነገሠው፣ የዳዊት ልጅ፣ የሰባኪው ቃል
ወይም የጕባኤ መሪ፤ እንዲሁም በ2 እና 12


2ሰባኪው፣
“ከንቱ፣ ከንቱ፣
የከንቱ ከንቱ፤
ሁሉም ነገር ከንቱ ነው” ይላል።

3ከፀሓይ በታች ከሚለፋበት ተግባር ሁሉ፣
ሰው ምን ትርፍ ያገኛል?
4ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤
ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።
5ፀሓይ ትወጣለች፤ ትጠልቃለችም፤
ወደምትወጣበትም ለመመለስ ትጣደፋለች።
6ነፋስ ወደ ደቡብ ይነፍሳል፤
ወደ ሰሜንም ይመለሳል፤
ዞሮ ዞሮ ይሄዳል፤
ዘወትርም ወደ ዑደቱ ይመለሳል።
7ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳሉ፤
ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤
ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣
ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ።
8ሰው መናገር ከሚችለው በላይ፣
ነገሮች ሁሉ አድካሚ ናቸው፤
ዐይን ከማየት አይጠግብም፤
ጆሮም በመስማት አይሞላም።
9የነበረው ነገር እንደ ገና ይሆናል፤
የተደረገውም ተመልሶ ይደረጋል፤
ከፀሓይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም።
10ማንም፣ “እነሆ፤ ይህ አዲስ ነገር ነው!”
ሊል የሚችለው አንዳች ነገር አለን?
ቀድሞውኑ በዚሁ የነበረ ነው፤
ከእኛ በፊት የሆነ ነው።
11የቀድሞ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፤
ወደ ፊት የሚመጡትም ቢሆኑ፣
ከእነርሱ በኋላ በሚተኩት አይታወሱም።

ጥበብ ከንቱ ነው

12እኔ ሰባኪው፣ በኢየሩሳሌም የእስራኤል ንጉሥ ነበርሁ። 13ከሰማይ በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ ለማጥናትና ለመመርመር ራሴን አተጋሁ፤ አምላክ በሰዎች ላይ የጫነው እንዴት ያለ ከባድ ሸክም ነው! 14ከፀሓይ በታች የተደረገውን ነገር ሁሉ አየሁ፤ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

15የተጣመመው ሊቃና አይችልም፤
የሌለም ነገር ሊቈጠር አይችልም።
16እኔም በልቤ፣ “እነሆ፤ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከገዙት ከማንኛቸውም ይልቅ ታላቅ ሆኛለሁ፤ ጥበብም በዝቶልኛል፤ በብዙ ጥበብና ዕውቀት ተመክሮም ዐልፌአለሁ” አልሁ። 17ከዚያም የጥበብንና የእብደትን፣ የሞኝነትንም ነገር ለመገንዘብ ራሴን አተጋሁ፤ ይህም ነፋስን እንደ መከተል መሆኑን ተረዳሁ።

18ጥበብ ሲበዛ፣ ትካዜ ይበዛልና፤
ዕውቀት ሲጨምርም ሐዘን ይበዛል።
Copyright information for AmhNASV