Ecclesiastes 10
1የሞቱ ዝንቦች ሽቶን እንደሚያገሙ፣ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ያቀልላል።
2የጠቢብ ልብ ወደ ቀኝ፣
የሞኝ ልብ ግን ወደ ግራ ያዘነብላል።
3ሞኝ በጐዳና ሲሄድ ማስተዋል ይጐድለዋል፤
ጅል መሆኑንም ለማንም ይገልጻል።
4የገዥ ቍጣ በተነሣብህ ጊዜ፣
ስፍራህን አትልቀቅ፤
ትዕግሥት ታላቁን ጥፋት ጸጥ ያደርጋልና።
5ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፤
ይህም ከገዥ የሚወጣ ስሕተት ነው፤
6ሞኞች በብዙ የክብር ስፍራዎች ሲቀመጡ፣
ሀብታሞች ግን በዝቅተኛ ስፍራ ሆነዋል።
7መሳፍንት እንደ ባሮች በእግራቸው ሲሄዱ፣
ባሮች ፈረስ ላይ ተቀምጠው አይቻለሁ።
8ጕድጓድን የሚምስ ራሱ ይገባበታል፤
ቅጥርንም የሚያፈርስ እባብ ይነድፈዋል።
9ድንጋይ የሚፈነቅል ይጐዳበታል፤
ግንድንም የሚፈልጥ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።
10መጥረቢያ ቢደንዝ፣
ጫፉም ባይሳል፣
ብዙ ጕልበት ይጨርሳል፤
ብልኀት ግን ለውጤት ያበቃል።
11እባብ በድግምት ከመፍዘዙ በፊት ቢነድፍ፣
ለደጋሚው ምንም አይጠቅመውም።
12ከጠቢብ አፍ የሚወጣ ቃል ባለ ሞገስ ነው፤
ሞኝ ግን በገዛ ከንፈሩ ይጠፋል፤
13ቃሉ በመጀመሪያ ሞኝነት ነው፤
በመጨረሻም ደግሞ ክፉ እብደት ነው፤
14ሞኙም ቃልን ያበዛል።
የሚመጣውን የሚያውቅ የለም፤
ከእርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ማን ሊነግረው ይችላል?
15የሞኝ ሥራ ራሱን ያደክመዋል፤
ወደ ከተማ የሚወስደውንም መንገድ አያውቅም።
16አንቺ፣ ንጉሥሽ ልጅ ▼
▼ወይም አሽከር
የሆነ፣መሳፍንትሽም በጧት ግብዣ የሚያደርጉ ምድር ሆይ፤ ወዮልሽ!
17አንቺ ንጉሥሽ ከተከበረው ዘር የሆነ፣
ለመስከር ሳይሆን ለብርታት፣
በተገቢው ጊዜ የሚበሉ መሳፍንት ያሉሽ ምድር ሆይ፤ የተባረክሽ ነሽ፤
18ሰው ሰነፍ ከሆነ ጣራው ይዘብጣል፤
እጆቹም ካልሠሩ ቤቱ ያፈስሳል።
19ግብዣ ለሣቅ ያዘጋጃል፤
ወይንም ሕይወትን ያስደስታል፤
ገንዘብም ካለ ሁሉ ነገር አለ።
20በዐሳብህም እንኳ ንጉሥን አትንቀፍ፤
በመኝታ ክፍልህም ባለጠጋን አትርገም፤
የሰማይ ወፍ ቃልህን ልትወስድ፣
የምትበረዋም ወፍ የምትለውን ልታደርስ ትችላለችና።
Copyright information for
AmhNASV