Ecclesiastes 2
ምድራዊ ደስታ ከንቱ ነው
1እኔም በልቤ፣ “መልካም የሆነውን ለማወቅ፣ በተድላ እፈትንሃለሁ” አልሁ፤ ነገር ግን ያም ከንቱ ነበረ። 2ደግሞም፣ “ሣቅ ሞኝነት ነው፤ ተድላስ ምን ይጠቅማል?” አልሁ። 3አሁንም አእምሮዬ በጥበብ እየመራኝ ራሴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት፣ ሞኝነትንም ለመያዝ ሞከርሁ፤ ሰዎች በዐጭር የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ባለው ላይ ቢሠሩት ሊጠቅማቸው የሚችል ምን እንደ ሆነ ለማየት ፈለግሁ።4ታላላቅ ነገሮችን አከናወንሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይንንም ተከልሁ፤ 5አትክልትን ተከልሁ፤ የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ላይ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶችን ሁሉ ተከልሁባቸው፤ 6የሚለመልሙ ዛፎችን፣ ለቦይ የሚሆኑ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ሠራሁ። 7ወንድና ሴት ባሪያዎችን ገዛሁ፤ በቤቴም የተወለዱ ሌሎች ባሪያዎች ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ይልቅ ብዙ የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች ነበሩኝ። 8ለራሴም ብርንና ወርቅን፣ የነገሥታትና የአውራጃዎችን ሀብት አካበትሁ፤ ወንድና ሴት አዝማሪዎች፣ የሰው መደሰቻ የሆኑ ቅምጦች ▼
▼በዕብራይስጥ የዚህ ሐረግ ትርጕም አይታወቅም
ነበሩኝ። 9ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሆንሁ፤ በዚህ ሁሉ ጥበቤ ከእኔ ጋር ነበረች። 10ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም፤
ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም፤
ልቤ በሠራሁት ሁሉ ደስ አለው፤
ይህም የድካሜ ሁሉ ዋጋ ነበረ።
11ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣
ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣
ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤
ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም።
ጥበብና ሞኝነት ከንቱ ናቸው
12ከዚያም ጥበብን፣እብደትንና ሞኝነትን ለመመርመር ሐሳቤን መለስሁ፤
አስቀድሞ ከተደረገው በቀር፣
ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል?
13ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ ሁሉ፣
ጥበብም ከሞኝነት እንደሚበልጥ ተመለከትሁ።
14የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤
ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል፤
ሆኖም የሁለቱም ዕድል ፈንታ፣
አንድ መሆኑን ተገነዘብሁ።
15ከዚያም በልቤ፣
“የሞኙ ዕድል ፈንታ በእኔም ላይ ይደርሳል፤
ታዲያ ጠቢብ በመሆኔ ትርፌ ምንድን ነው?” አልሁ።
በልቤም፣
“ይህም ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ።
16ጠቢቡም ሰው እንደ ሞኙ ለዘላለም አይታወስምና፤
በሚመጡት ዘመናት ሁለቱም ይረሳሉ።
ለካ፣ ጠቢቡም እንደ ሞኙ መሞቱ አይቀርም!
ጥረት ከንቱ ነው
17ስለዚህ ከፀሓይ በታች የሚሠራው ሥራ አሳዛኝ ስለ ሆነብኝ ሕይወትን ጠላሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 18ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው የግድ እተውለታለሁና። 19እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከፀሓይ በታች ድካሜንና ችሎታዬን ባፈሰስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 20ስለዚህ ከፀሓይ በታች በደከምሁበት ነገር ሁሉ ላይ ልቤ ተስፋ መቍረጥ ጀመረ፤ 21ምክንያቱም ሰው ሥራውን በጥበብ፣ በዕውቀትና በብልኀት ሠርቶ፣ ከዚያ ያለውን ሁሉ ለሌላ ላልለፋበት ሰው ይተውለታል። ይህም ደግሞ ከንቱና ትልቅ ጕዳት ነው። 22ሰው ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ጥረትና ልፋት ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው? 23በዘመኑ ሁሉ ሥራው ሥቃይና ሐዘን ነው፤ በሌሊትም እንኳ ቢሆን አእምሮው አያርፍም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።24ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደሚሰጥ አየሁ፤ 25ከእርሱ ዘንድ ካልሆነ ማን መብላትና መደሰት ይችላል? 26እግዚአብሔር፣ ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብን፣ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል። ለኀጢአተኛ ግን፣ እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ይተውለት ዘንድ፣ ሀብትን የመሰብሰብና የማከናወን ተግባር ይሰጠዋል። ይህም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
Copyright information for
AmhNASV