Ecclesiastes 4
ግፍ፣ ጥረት፣ ብቸኝነት
1እንደ ገና ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ አስተዋልሁም፤የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤
የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤
ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ፤
የሚያጽናናቸውም አልነበረም።
2እኔም የቀድሞ ሙታን፣
ዛሬ በሕይወት ካሉት ሕያዋን ይልቅ፣
ደስተኞች እንደ ሆኑ ተናገርሁ።
3ነገር ግን ከሁለቱም ይልቅ፣
ገና ያልተወለደው፣
ከፀሓይ በታች የሚደረገውንም፣
ክፋት ያላየው ይሻላል።
4እንዲሁም ጥረትና የሥራ መከናወን ሁሉ ሰው በባልንጀራው ላይ ካለው ቅናት እንደሚመነጭ ተመለከትሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
5ሰነፍ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል፤
የገዛ ራሱንም ሥጋ ይበላል።
6በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣
በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል።
7ደግሞም ከፀሓይ በታች ከንቱ የሆነን ነገር አየሁ፤
8ልጅም ሆነ ወንድም የሌለው፣
ብቸኛ ሰው አለ፤
ጥረቱ ማለቂያ የለውም፤ ዐይኑም ባለው ሀብት ገና አልረካም፤
እርሱም፣ “ለማን ብዬ ነው የምደክመው?
ራሴን ከማስደሰትስ የምቈጠበው
ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ፤
ይህም ደግሞ ከንቱ፣ የጭንቅ ኑሮ ነው።
9ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣
ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤
10አንዱ ቢወድቅ፣
ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል።
ቢወድቅ የሚያነሣው ረዳት የሌለው ግን፣
እንዴት አሳዛኝ ነው!
11ደግሞም ሁለቱ አብረው ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤
ነገር ግን አንዱ ብቻውን እንዴት ሊሞቀው ይችላል?
12አንድ ሰው ብቸኛውን ቢያጠቃውም፣
ሁለት ከሆኑ ይመክቱታል፤
በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም።
በልጦ መገኘት ከንቱ ነው
13ምክርን መቀበል ከማያውቅ ሞኝና ሽማግሌ ንጉሥ ይልቅ ጠቢብ የሆነ ድኻ ወጣት ይሻላል። 14ወጣቱ ከእስር ቤት ወደ ንጉሥነት የመጣ ወይም በግዛቱ ውስጥ በድኽነት የተወለደ ሊሆን ይችላል። 15ከፀሓይ በታች የሚኖሩና የሚመላለሱ ሁሉ፣ ንጉሡን የሚተካውን ወጣት ተከትለውት አየሁ። 16በፊቱ የነበረው ሕዝብ ሁሉ ቍጥር ስፍር አልነበረውም፤ ከእርሱ በኋላ የመጡት ግን በተተኪው አልተደሰቱም። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
Copyright information for
AmhNASV