‏ Ephesians 2

በክርስቶስ ሕያው መሆን

1እናንተ በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ 2በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር። 3እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት
ወይም የአሮጌውን ባሕርይ ፈቃድ
እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን።
4ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ 5በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው። 6እግዚአብሔርም ከክርስቶስ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን፤ 7ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው፤ 8በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ 9ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም፤ 10ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራ እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።

በክርስቶስ አንድ መሆን

11ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የሆናችሁ፣ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፣ ራሳቸውን “ተገርዘናል” በሚሉት፣ “ያልተገረዙ” የተባላችሁ ያን አስታውሱ፤ 12በዚያን ዘመን ከክርስቶስ ተለይታችሁ፣ ከእስራኤል ወገንነት ርቃችሁ፣ ለኪዳኑም ተስፋ ባዕዳን ሆናችሁ፣ በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። 13አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።

14ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤ 15ሕግንም፣ ከትእዛዞቹና ከሥርዐቱ ጋር በሥጋው ሻረ። ዐላማውም ከሁለቱ አንድን አዲስ ሰው በራሱ ፈጥሮ ሰላምን ለማድረግ ነው። 16ጥልን በገደለበት በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ። 17መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተ፣ ቀርበው ለነበሩትም ለእነርሱ ሰላምን ሰበከ፤ 18ሁላችንም በእርሱ አማካይነት በአንዱ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለንና።

19ከዚህ የተነሣ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተ ሰብ አባል ናችሁ እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲህ መጻተኞችና እንግዶች አይደላችሁም። 20በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤ 21በእርሱ ሕንጻ ሁሉ አንድ ላይ ተገጣጥሞ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል። 22እናንተም ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ ትሆኑ ዘንድ አብራችሁ እየተገነባችሁ ነው።

Copyright information for AmhNASV