Esther 7
ሐማ ተሰቀለ
1ስለዚህ ንጉሡና ሐማ ከንግሥት አስቴር ጋር ለመጋበዝ ሄዱ፤ 2በሁለተኛውም ቀን የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ፣ ንጉሡ እንደ ገና፣ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ የምትለምኚው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ የምትጠይቂውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል” አላት።3ከዚያም ንግሥት አስቴር እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼና ግርማዊነትህን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፣ ሕይወቴን ታደጋት፤ ልመናዬ ይህ ነው፤ ሕዝቤን አትርፍ፤ ጥያቄዬም ይኸው ነው። 4እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለዕርድና ለመደምሰስ ተሸጠናልና። ወንዶችና ሴቶች ባሮች ለመሆን የተሸጥን ቢሆን ኖሮ፣ ዝም ባልሁ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ጭንቀት ንጉሡን ለማስቸገር የሚበቃ አይደለም ▼
▼ወይም፣ ዝም ባልሁም ነበር፤ ነገር ግን ባለጋራችን የሚሰጠው ካሣ ንጉሡ ከሚያጣው ነገር ጋር ከቶ አይነጻጸርም
።” 5ንጉሥ ጠረክሲስም ንግሥት አስቴርን፣ “ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እስከዚህ የደፈረውስ ሰው የታለ?” ሲል ጠየቀ።
6አስቴርም፣ “ያ ባላጋራና ጠላት ይህ ክፉው ሐማ ነው” አለች።
ከዚያም ሐማ በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት እጅግ ደነገጠ። 7ንጉሡ ከተቀመጠበት በቍጣ ተነሣ፤ የወይን ጠጁንም ትቶ ወደ ቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ሄደ። ሐማ ግን ንጉሡ ሊያጠፋው ቈርጦ መነሣቱን ስላወቀ፣ ንግሥት አስቴር ሕይወቱን እንድታተርፍለት ለመማጠን በዚያው ቀረ።
8ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ሲመለስ አስቴር ደገፍ ባለችበት ድንክ ዐልጋ ላይ ሐማ ተደፍቶ ነበር።
ንጉሡም፣ “ይባስ ብሎ አብራኝ ያለችውን ንግሥት በገዛ ቤቴ ሊደፍራት ያስባልን?” ሲል ተናገረ።
ይህ ቃል ከንጉሡ አፍ ገና እንደ ወጣ፣ የሐማን ፊት ሸፈኑት። 9ከዚያም ንጉሡን በቅርብ ከሚያገለግሉት ጃንደረቦች አንዱ የሆነው ሐርቦና፣ “እነሆ ቁመቱ አምሳ ክንድ ▼
▼23 ሜትር ያህል ነው።
የሆነ ግንድ በሐማ ቤት አጠገብ ተተክሏል፤ ይህን ያዘጋጀው ንጉሡን ለማዳን በጎ ነገር ለተናገረው ለመርዶክዮስ ነው” አለ።ንጉሡም፣ “በዚሁ ላይ ስቀሉት” አለ። 10ስለዚህ ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሐማን ሰቀሉት፤ ከዚያም የንጉሡ ቍጣ በረደ።
Copyright information for
AmhNASV