‏ Ezekiel 2

የሕዝቅኤል መጠራት

1እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ እኔም እናገርሃለሁ” አለኝ። 2እርሱም ሲናገር፣ መንፈስ ወደ ውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ ሲናገረኝም ሰማሁት።

3እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእኔ ላይ ወደ ዐመፀው ወደ ዐመፀኛው የእስራኤል ሕዝብ እልክሃለሁ፤ እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐምፀውብኛል። 4ሕዝቡም እልኸኛና ዐንገተ ደንዳና ነው፤ እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ በላቸው። 5እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለሆኑ፤ ቢሰሙም ባይሰሙም በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበር ያውቃሉ። 6አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱን ወይም ቃላቸውን አትፍራ፤ ኵርንችትና እሾኽ በዙሪያህ ቢኖሩም፣ በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም አትፍራ። እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም፣ አንተ በሚሉህ ነገር አትፍራ፤ እነርሱም አያስደንግጡህ። 7እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለሆኑ፣ ቢሰሙም ባይሰሙም አንተ ቃሌን ንገራቸው። 8አንተ ግን የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምልህን ስማ፤ እንደዚያ ዐመፀኛ ቤት ዐታምፅ፤ አፍህን ክፈት፤ የምሰጥህንም ብላ።”

9ከዚህም በኋላ፣ እነሆ አንድ እጅ ወደ እኔ ተዘርግቶ አየሁ፤ ጥቅልል መጽሐፍም ነበረበት፤ 10እርሱም በፊቴ ዘረጋው፤ መጽሐፉም ከፊትና ከኋላው የሰቈቃ፣ የልቅሶና የዋይታ ቃላት ተጽፎበት ነበር።

Copyright information for AmhNASV