Ezekiel 5
1“አንተም፤ የሰው ልጅ ሆይ፤ የተሳለ ሰይፍ ወስደህ እንደ ጢም መላጫ ጠጕርህንና ጢምህን ተላጭበት፤ ጠጕሩንም በሚዛን ከፋፍል። 2የከበባው ጊዜ ሲፈጸም የጠጕሩን ሢሶ በከተማው ውስጥ አቃጥለው፤ ሌላውን ሢሶ ጠጕር በከተማዪቱ ዙሪያ ሁሉ በሰይፍ ቈራርጠው፤ የቀረውንም ሢሶ ደግሞ ለነፋስ በትነው፤ እኔም በተመዘዘ ሰይፍ አሳድዳቸዋለሁና። 3ደግሞም ከጠጕሮቹ ጥቂት ወስደህ በመጐናጸፊያህ ጫፍ ቋጥር፤ 4እንደገናም ከእነዚህ ጥቂት ወስደህ እሳት ውስጥ ጨምራቸው፤ አቃጥላቸውም። እሳትም ከዚያ ወጥቶ ወደ እስራኤል ቤት ሁሉ ይሠራጫል።5“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አገሮችን በዙሪያዋ ሁሉ አድርጌ፣ በአሕዛብም መካከል ያስቀመጥኋት ኢየሩሳሌም ይህች ናት። 6እርሷም በዙሪያዋ ካሉት አገሮችና አሕዛብ ይልቅ በሕጌና በሥርዐቴ ላይ በክፋቷ ዐመፀች፤ ሕጌን ጥላለች፤ ሥርዐቴንም አልተከተለችም።’
7“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብ ይልቅ ሞገደኞች ሆናችኋል፤ ሥርዐቴን አልተከተላችሁም፤ ለሕጌም አልታዘዛችሁም። በዙሪያችሁ የሚገኙ አሕዛብ የሚጠብቁትን ሕግ እንኳ አልጠበቃችሁም።’ ▼
▼አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆችና አንዳንድ የዕብራይስጥና የሱርስት የጥንት ቅጆች የሚጠብቁትን ሕግ ጠብቃችኋል ይላሉ።
8“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፤ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በአሕዛብም ፊት ፍርድ አመጣብሻለሁ። 9በጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ምክንያት ካሁን ቀደም ያላደረግሁትን፣ ወደ ፊትም የማላደርገውን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ። 10ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን፣ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አመጣብሻለሁ፤ ከአንቺ የተረፉትንም ለነፋስ እበትናለሁ።’ 11ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ መቅደሴን በረከሱ ምስሎችሽና በጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ስላጐደፍሽ፣ ፊቴን ከአንቺ እመልሳለሁ፤ በርኅራኄ አልመለከትሽም፤ አልምርሽም። 12ከሕዝብሽ ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፤ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሌላው ሢሶ ከቅጥርሽ ውጪ በሰይፍ ይወድቃል፤ የቀረውን ሢሶ ደግሞ ለነፋስ እበትናለሁ፤ በተመዘዘም ሰይፍ አሳድደዋለሁ።
13“ከዚያም ቍጣዬ ይበርዳል፤ በእነርሱ ላይ የመጣው መቅሠፍቴ ይመለሳል፤ ስበቀላቸው እረካለሁ፤ በእነርሱም ላይ መዓቴን ካወረድሁ በኋላ፣ እኔ እግዚአብሔር በቅናት እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።
14“በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ መካከል፤ በአጠገብሽም በሚያልፉ ሁሉ ፊት ባድማና መሳለቂያ አደርግሻለሁ። 15በቍጣና በመዓት፣ እንዲሁም በጭካኔ ፍርድ በማመጣብሽ ጊዜ፣ በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ ዘንድ የመሣቂያና የመሣለቂያ፣ የተግሣጽና የማስደንገጫ ምልክት ትሆኛለሽ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ። 16የሚገድለውንና አጥፊ የሆነውን የራብ ፍላጻ በእናንተ ላይ በምወረውርበት ጊዜ በርግጥ ላጠፋችሁ እሰድዳለሁ። በራብ ላይ ራብ አመጣባችኋለሁ፤ የምግብ ምንጫችሁንም አደርቃለሁ። 17ራብንና የዱር አራዊትን እሰድድባችኋለሁ፤ እነርሱም ልጅ አልባ ያደርጓችኋል። ቸነፈርና ደም መፋሰስ ያጥለቀልቃችኋል፤ ሰይፍንም አመጣባችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”
Copyright information for
AmhNASV