James 2
አድልዎ ማድረግ አይገባም
1ወንድሞቼ ሆይ፤ ክቡር በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ እንደ መሆናችሁ አድልዎ አታድርጉ። 2የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፣ 3ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፣ “ለአንተ የሚሆን መልካም ስፍራ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፣ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፣ 4በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን?5የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወድዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? 6እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን? 7በእናንተ የተጠራውን ክቡር የሆነውን ስም የሚሳደቡ እነርሱ አይደሉምን?
8በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ፣ መልካም እያደረጋችሁ ነው። 9አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው፤ በሕግም ፊት እንደ ሕግ ተላላፊዎች ትቈጠራላችሁ፤ 10ምክንያቱም ሕግን ሁሉ የሚፈጽም ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ቢኖር፣ ሁሉን እንደ ተላለፈ ይቈጠራል። 11“አታመንዝር” ያለ እርሱ ራሱ “አትግደልም” ብሏልና። ባታመነዝር፣ ነገር ግን ብትገድል፣ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል።
12ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ ነጻነት በሚሰጠው ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች ሁኑ፤ 13ምክንያቱም ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል።
እምነትና ሥራ
14ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል፣ ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን? 15አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ ዐጥተው፣ 16ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል? 17እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።18ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ።”
እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። 19አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ።
20አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው ▼
▼አንዳንድ ጥንታዊ ያልሆኑ ቅጆች፣ ሙት ይሉታል።
መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን? 21አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? 22በዚህም፣ እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደ ነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ። 23“አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ። 24እንግዲህ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። 25እንዲሁም ጋለሞታዪቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? 26ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ፣ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው።
Copyright information for
AmhNASV