‏ John 15

የወይን ግንድና ቅርንጫፎቹ

1 “እውነተኛው የወይን ተክል እኔ ነኝ፤ አትክልተኛውም አባቴ ነው። 2እርሱም በእኔ ያለውን፣ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቈርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን የበለጠ እንዲያፈራ ይገርዘዋል።
ይገርዘዋል የሚለው የግሪኩ ቃል ያጠራዋል የሚል ትርጕም አለው።
3ከነገርኋችሁ ቃል የተነሣ እናንተ አሁን ንጹሓን ናችሁ። 4በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም።

5 “እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በእርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና። 6በእኔ የማይኖር ተጥሎ እንደሚደርቅ ቅርንጫፍ ነው፤ እንዲህ ያሉት ቅርንጫፎች ተለቅመው ወደ እሳት ይጣላሉ፤ ይቃጠላሉም። 7በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ፤ ይሰጣችኋልም። 8ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብትገልጡ፣ በዚህ አባቴ ይከብራል።

9 “አብ እንደ ወደደኝ ሁሉ እኔም ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። 10እኔ የአባቴን ትእዛዝ ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር፣ እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ። 12ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። 13ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም፤ 14የማዝዛችሁን ብትፈጽሙ ወዳጆቼ ናችሁ። 15ከእንግዲህ አገልጋዮች አልላችሁም፤ አገልጋይ ጌታው የሚሠራውን አያውቅምና፤ ነገር ግን ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ገለጽሁላችሁ ወዳጆች ብያችኋለሁ። 16እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ እንድትሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ ፍሬያችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። ስለዚህም አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። 17እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ፣ ትእዛዜ ይህች ናት።

ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ

18 “ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። 19ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደ ሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለዚሁ ነው። 20‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳድደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነም ቃላችሁን ይጠብቃሉ። 21የላከኝን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ያደርጉባችኋል። 22መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም። 23እኔን የሚጠላ፣ አባቴንም ይጠላል። 24ሌላ ሰው ያላደረገውን በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ፣ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እነዚህን ታምራት አይተዋል፤ ሆኖም እኔንም አባቴንም ጠልተዋል። 25ይህም፣ ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው።

26 “እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። 27እናንተም ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ከእኔ ጋር ስለ ነበራችሁ፣ ትመሰክራላችሁ።

Copyright information for AmhNASV