Joshua 17
1ምናሴ የዮሴፍ የበኵር ልጅ እንደ መሆኑ መጠን፣ ለነገዱ የተመደበለት ድርሻ ይህ ነበር፤ የምናሴ የበኵር ልጅ ማኪር፣ የገለዓዳውያን አባት ብርቱ ጦረኛ ስለ ነበር ገለዓድና ባሳን ድርሻው ሆኑ። 2ስለዚህ ይህ ርስት ለተቀሩት የምናሴ ዘሮች ማለትም ለአቢዔዝር፣ ለኬሌግ፣ ለአሥሪኤል፣ ለሴኬም፣ ለኦፌር፣ ለሸሚዳ ጐሣዎች የተሰጠ ነው፤ እነዚህ በየጐሣዎቻቸው የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ሌሎች ወንዶች ዝርያዎች ናቸው።3ሰለጰዓድ የአፌር ልጅ፣ የገለዓድ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የምናሴ ልጅ ነው። እርሱም ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም። የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፣ ኑዓ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ቲርጻ ይባላል። 4እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ መሪዎቹ ቀርበው፣ “ከወንድሞቻችን ጋር ርስት እንድንካፈል እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞታል” አሏቸው። ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከአባታቸው ወንድሞች ጋር ርስት ሰጣቸው። 5ምናሴም ከገለዓድና ከባሳን ምድር ሌላ፣ ዐሥር ቦታ የሚደለደል የመሬት ክፍል በዮርዳኖስ ምሥራቅ ነበረው፤ 6የምናሴ ነገድ ሴት ልጆች ከወንዶቹ ጋር ርስት ተካፍለዋልና። የገለዓድ ምድር ግን ለቀሩት የምናሴ ዘሮች ተሰጠ።
7የምናሴ ርስት ከአሴር አንሥቶ ከሴኬም በስተ ምሥራቅ እስካለችው እስከ ሚክምታት ይደርሳል፤ ድንበሩም ወደ ደቡብ በመዝለቅ በዓይንታጱዋ የሚኖረውን ሕዝብ ይጨምራል። 8የታጱዋ ምድር የምናሴ ይዞታ ነበር፤ ይሁን እንጂ በድንበሩ ላይ የምትገኘው የታጱዋ ከተማ የኤፍሬም ዘሮች ይዞታ ነበረች። 9ከዚያም በመቀጠል ድንበሩ በደቡብ በኩል ወደ ቃና ወንዝ ይደርሳል። በምናሴ ከተሞችም መካከል የኤፍሬም ከተሞች ነበሩ፤ ያም ሆኖ የምናሴ ድንበር የወንዙ ሰሜናዊ ክፍል ሲሆን፣ እስከ ባሕሩ ይዘልቃል። 10በደቡብ በኩል ያለው ምድር የኤፍሬም ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ያለው ደግሞ የምናሴ ነበር፤ የምናሴ ግዛት እስከ ባሕሩ የሚደርስ ሲሆን፣ ሰሜናዊ ድንበሩ አሴር፣ ምሥራቃዊ ድንበሩ ደግሞ ይሳኮር ነው።
11እንዲሁም በይሳኮርና በአሴር ውስጥ ቤትሳን፣ ይብልዓም፣ የዶር ሕዝብ፣ ዐይን ዶር፣ ታዕናክና መጊዶ በዙሪያቸው ካሉ ሰፈሮቻቸው ጋር የምናሴ ነበሩ፤ ሦስተኛውም ናፎት ነው ▼
▼ይኸውም ናፎት ዶር ነው።
። 12ይሁን እንጂ የምናሴ ዘሮች እነዚህን ከተሞች መያዝ አልቻሉም፤ ከነዓናውያን የያዙትን ላለመልቀቅ ቍርጥ ሐሳብ አድርገው ነበርና። 13እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ከዚያ ፈጽመው አላባረሯቸውም ነበር።
14የዮሴፍ ዘሮች ኢያሱን፣ “ቍጥራችን ብዙ ነው፤ እግዚአብሔርም አብዝቶ ባርኮናል፤ ታዲያ እንዴት ርስታችን አንድ ዕጣና አንድ ድርሻ ብቻ ሆነ?” አሉት።
15ኢያሱም መልሶ፣ “ቍጥራችሁ ይህን ያህል በዝቶ ኰረብታማው የኤፍሬም ምድር እስከዚህ የሚጠባችሁ ከሆነ፣ ወደ ፌሪዛውያንና ወደ ራፋይም ምድር ወጥታችሁ ደኑን ለራሳችሁ መንጥሩ” አላቸው።
16የዮሴፍም ዘሮች፣ “ኰረብታማው አገር አይበቃንም፤ ደግሞም በሜዳው ላይ ያሉት በቤትሳንና በሰፈሮቿ፣ እንዲሁም በኢይዝራኤል ሸለቆ የሚኖሩት ከነዓናውያን ሁሉ የብረት ሠረገሎች አሏቸው” አሉት።
17ኢያሱ ግን ለዮሴፍ ዘሮች ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ቍጥራችሁ ብዙ፣ እጅግም ኀያል እንደ መሆናችሁ ድርሻችሁ አንድ ብቻ አይሆንም፤ 18ነገር ግን ደን የለበሰው ኰረብታማው አገር የእናንተ ነው፤ ሄዳችሁ መንጥሩት፣ ዳር ድንበሩ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ከነዓናውያን የብረት ሠረገላ ቢኖራቸውና ብርቱዎች ቢሆኑም እንኳ ከዚያ ታስወጧቸዋላችሁ።”
Copyright information for
AmhNASV