Joshua 3
እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ተሻገሩ
1ኢያሱም ማልዶ ተነሣ። ከእስራኤላውያንም ሁሉ ጋር ከሰጢም ወደ ዮርዳኖስ መጥተው ወንዙን ከመሻገራቸው በፊት በዚያ ሰፈሩ። 2ከሦስት ቀን በኋላም የጦሩ አለቆች በሰፈር ውስጥ ዐለፉ፤ 3ሕዝቡንም እንዲህ ሲሉ አዘዙ፤ “ሌዋውያን ካህናቱ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ፣ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ታቦቱን ተከተሉ፤ 4ከአሁን በፊት በዚህ መንገድ ሄዳችሁ ስለማታውቁ፤ በየት በኩል መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ፤ ሆኖም በታቦቱና በእናንተ መካከል የሁለት ሺሕ ክንድ ▼▼የዕብራይስጡ ትርጕም 900 ሜትር ይላል።
ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱም አትቅረቡ።” 5ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን፣ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር በመካከላችሁ አስደናቂ ነገር ስለሚያደርግ ራሳችሁን ቀድሱ” አላቸው።
6ኢያሱም ካህናቱን፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ ሕዝቡን ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ታቦቱን ተሸክመው ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ።
7 እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ፣ በእስራኤል ሁሉ ፊት አንተን ከፍ ከፍ ማድረጌን በዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። 8የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትንም ካህናት፣ ‘ከዮርዳኖስ ውሃ ዳር ስትደርሱ፣ በወንዙ ውስጥ ገብታችሁ ቁሙ’ በላቸው።”
9ኢያሱ የእስራኤልን ሕዝብ “ወደዚህ ቀርባችሁ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ አላቸው፤ 10እንግዲህ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ መሆኑንና እርሱም በርግጥ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ኤዊያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ እንዴት አድርጎ እንደሚያሳድዳቸው የምታውቁት በዚህ ነው። 11እነሆ፤ የምድር ሁሉ ጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት ቀድሟችሁ ወደ ዮርዳኖስ ይገባል። 12እንግዲህ ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰው ምረጡ፤ ከየነገዱም አንዳንድ ሰው ይሁን። 13የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ገና እግራቸውን በዮርዳኖስ ውሃ ውስጥ እንዳስገቡ፣ ቍልቍል የሚወርደው ውሃ ወዲያውኑ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል።”
14ስለዚህ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ሰፈሩን ለቀው ሲወጡ፣ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከፊታቸው ቀድመው ሄዱ። 15ወቅቱም የመከር ጊዜ በመሆኑ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ነበር፤ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግራቸው ውሃውን እንደ ነካ፣ 16ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ “አዳም” ተብላ እስከምትጠራው ሩቅ ከተማ ድረስ በመከማቸት እንደ ክምር ተቈለለ፤ ቍልቍል ወደ ዓረባ ጨው ባሕር ▼
▼የሙት ባሕር ነው።
የሚወርደውም ውሃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም ከኢያሪኮ ትይዩ ባለው አቅጣጫ ተሻገሩ። 17የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናትም፣ ሕዝቡ ሁሉ፣ ማለት እስራኤል በሙሉ ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል በደረቁ ምድር ላይ ቀጥ ብለው ቆመው ነበር።
Copyright information for
AmhNASV