‏ Joshua 5

በጌልገላ የተደረገ ግዝረት

1በዚህ ጊዜ ከዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ያሉት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ፣ በባሕሩም ዳርቻ ያሉ የከነዓናውያን ነገሥታት በሙሉ እግዚአብሔር ዮርዳኖስን እስክንሻገር ወንዙን በእስራኤላውያን ፊት እንዴት እንዳደረቀው በሰሙ ጊዜ፣ ልባቸው በፍርሀት ቀለጠ፤ እስራኤላውያንንም ለመቋቋም ድፍረት ዐጡ።

2በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “የባልጩት መቍረጫ አዘጋጅተህ፣ ያልተገረዙትን እስራኤላውያንን ለሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው” አለው። 3ስለዚህ ኢያሱ የባልጩት መቍረጫ አዘጋጅቶ በጊብዓዝ ዓረሎት
ትርጓሜውም የሸለፈት ኰረብታ ማለት ነው።
በተባለ ስፍራ እስራኤላውያንን ገረዛቸው።

4እንግዲህ ኢያሱ እስራኤላውያንን የገረዘበት ምክንያት ይህ ነው፤ ዕድሜያቸው መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ ሞቱ። 5ከዚያ የወጡት ሰዎች ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ በጕዞ ላይ ሳሉ የተወለዱት ግን በሙሉ አልተገረዙም ነበር። 6ግብፅን ለቀው በወጡ ጊዜ መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፣ እነርሱ ሞተው እስኪያልቁ ድረስ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይንከራተቱ ነበር። እግዚአብሔር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው ቃል የገባላቸውን ያችን ማርና ወተት የምታፈስስ ምድር እንደማያዩአት ምሏልና። 7ስለዚህ በእነርሱ ምትክ ወንዶች ልጆቻቸውን አስነሣ። እንግዲህ ኢያሱ የገረዛቸው እነዚህን ነበር፤ በጕዞ ላይ ሳሉ ባለመገረዛቸው ከነሸለፈታቸው ነበሩና። 8ሕዝቡ ሁሉ ከተገረዙ በኋላ ቍስሉ እስኪሽር ድረስ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ቈዩ።

9ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነሆ፤ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ” አለው፤ ከዚህም የተነሣ የዚያ ቦታ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ
በዕብራይስጡ ጌልገላ የሚለው ቃል ድምፅ መንከባለል ከሚለው ቃል ጋር አንድ ዐይነት ነው።
ተባለ።

10እስራኤላውያን በኢያሪኮ ሜዳ በጌልገላ ሰፍረው ሳሉ፣ ወሩ በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የፋሲካን በዓል አከበሩ። 11ከፋሲካም በኋላ በዚያኑ ዕለት የምድሪቱን ፍሬ ማለት ያልቦካ ቂጣና የተጠበሰ እሸት በሉ። 12የምድሪቱን ፍሬ በበሉበት ቀን
ወይም በበሉበት ጊዜ ተብሎ መተርጐም ይችላል።
መናው መውረዱ ቀረ፤ ከዚያ በኋላ ለእስራኤላውያን መና አልወረደላቸውም፤ ነገር ግን በዚያኑ ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።

የኢያሪኮ መውደቅ

13ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ፣ ቀና ብሎ ሲመለከት የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ አንድ ሰው ከፊቱ ቆሞ አየ። ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፤ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ሲል ጠየቀው።

14እርሱም፣ “አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃ በመሆኔ እነሆ፤ መጥቻለሁ” ሲል መለሰለት፤ ኢያሱም በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደና፣ “ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድን ነው?” አለው።

15 የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃም ኢያሱን፣ “ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፤ የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ናትና” አለው፤ ኢያሱም እንደ ታዘዘው አደረገ።

Copyright information for AmhNASV