Matthew 17
የኢየሱስ መልክ በቅጽበት መቀየር
17፥1-8 ተጓ ምብ – ሉቃ 9፥28-36 17፥1-13 ተጓ ምብ – ማር 9፥2-13 1ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ረዥም ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ።2በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። 3ወዲያውም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።
4ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፤ በዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው።
5እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።
6ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲሰሙ ደንግጠው በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። 7ኢየሱስም ቀርቦ ነካቸውና፣ “ተነሡ፤ አትፍሩ” አላቸው። 8ቀና ብለው ሲመለከቱም ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንንም አላዩም።
9ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም እንዳትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው።
10ደቀ መዛሙርቱም፣ “ታዲያ የኦሪት ሕግ መምህራን፣ ኤልያስ አስቀድሞ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
11እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ መጥቶ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፤ 12ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ መጥቷል፤ ሆኖም የፈለጉትን ነገር አደረጉበት እንጂ አላወቁትም። እንዲሁም የሰው ልጅ በእጃቸው መከራን ይቀበላል።” 13በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ተረዱ።
ኢየሱስ የሚጥል በሽታ ያለበትን ልጅ ፈወሰ
14ወደ ሕዝቡ እንደ ተመለሱ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና እንዲህ አለ፤ 15“ጌታ ሆይ፤ እባክህ ልጄን ማርልኝ፤ በሚጥል በሽታ እጅግ እየተሠቃየ ነው፤ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥ ይወድቃል፤ ውሃ ውስጥም ይገባል፤ 16ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።”17ኢየሱስም፣ “አንት የማታምን ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤ እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ። ልጁን ወደዚህ አምጡት” አለ። 18ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸውና ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነ።
19ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛ ጋኔኑን ማስወጣት ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
20እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤ 21የዚህ ዐይነቱ ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በስተቀር አይወጣም።” ▼
▼አንዳንድ የጥንት ቅጆች ቍ 21 የላቸውም።
22በገሊላ ተሰባስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “የሰውን ልጅ አሳልፈው ለሰዎች ይሰጡታል፤ 23ይገድሉታልም፤ እርሱም በሦስተኛው ቀን ይነሣል።” ደቀ መዛሙርቱም እጅግ ዐዘኑ።
ስለ ቤተ መቅደስ ግብር ክፍያ
24ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱ ግብር ተቀባዮች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው “መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር የቤተ መቅደስ ግብር አይከፍልምን?” አሉት።25እርሱም፣ “ይከፍላል እንጂ” አላቸው።
ጴጥሮስ ወደ ቤት እንደ ገባ ኢየሱስ በቅድሚያ፣ “ስምዖን፤ የምድር ነገሥታት ግብር ወይም ቀረጥ የሚቀበሉት ከራሳቸው ልጆች ወይስ ከሌሎች ይመስልሃል?” አለው።
26ጴጥሮስም፣ “ከሌሎች ነው የሚቀበሉት” አለው።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “እንግዲያውስ ልጆች ነጻ ናቸው፤ 27ሆኖም እንዳናስቀይማቸው ሄደህ መንጠቈህን ወደ ባሕር ጣል፤ መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት የምታገኘውን አንድ እስታቴር በእኔና በአንተ ስም ክፈል።”
Copyright information for
AmhNASV