Proverbs 13
1ጠቢብ ልጅ የአባቱን ምክር በማስተዋል ይሰማል፤ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አያዳምጥም።
2ሰው ከከንፈሩ ፍሬ መልካም ነገር ያገኛል፤
ወስላቶች ግን ዐመፅን ይናፍቃሉ።
3አንደበቱን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፤
አፉ እንዳመጣለት የሚናገር ግን ይጠፋል።
4ሰነፍ አጥብቆ ይመኛል፤ አንዳችም አያገኝም፤
የትጉሆች ምኞት ግን ይረካል።
5ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤
ክፉ ሰው ግን ኀፍረትንና ውርደትን ያመጣል።
6ጽድቅ ቅን የሆነውን ሰው ትጠብቀዋለች፤
ክፋት ግን ኀጢአተኛውን ትጥለዋለች።
7ምንም ሳይኖረው ባለጠጋ መስሎ የሚታይ ሰው አለ፤
ሌላው ድኻ መስሎ ይታያል፤ ግን ብዙ ሀብት አለው።
8የሰው ሀብቱ ለሕይወቱ ቤዛ ሊሆነው ይችላል፤
ድኻው ግን ሥጋት የለበትም።
9የጻድቃን ብርሃን ደምቆ ይበራል፤
የክፉዎች መብራት ግን ይጠፋል።
10ትዕቢት ጠብን ብቻ ያስፋፋል፤
ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ትገኛለች።
11ያላግባብ የተገኘ ገንዘብ እየተመናመነ ያልቃል፤
ገንዘቡን ጥቂት በጥቂት የሚያከማች ግን ይጠራቀምለታል።
12ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል፤
የተሳካ ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ነው።
13ምክርን የሚያቃልል በራሱ ላይ ጥፋት ያመጣል፤
ትእዛዝን የሚያከብር ግን ወሮታን ይቀበላል።
14የጠቢብ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤
ሰውን በሞት ወጥመድ እንዳይያዝ ታደርገዋለች።
15መልካም ማስተዋል ሞገስን ታስገኛለች፤
የከዳተኞች መንገድ ግን አስቸጋሪ ነው። ▼
▼ወይም የከዳተኞች መንገድ ግን አይጸናም
16አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል፤
ተላላ ግን ሞኝነቱን ይገልጣል።
17ክፉ መልእክተኛ መከራ ውስጥ ይገባል፤
ታማኝ መልእክተኛ ግን ፈውስን ያመጣል።
18ተግሣጽን የሚንቅ ወደ ድኽነትና ኀፍረት ይሄዳል፤
ዕርምትን የሚቀበል ሁሉ ግን ይከበራል።
19ምኞት ስትፈጸም ነፍስን ደስ ታሰኛለች፤
ተላሎች ግን ከክፋት መራቅን ይጸየፋሉ።
20ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤
የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።
21መጥፎ ዕድል ኀጢአተኛን ይከታተላል፤
ብልጽግና ግን የጻድቃን ዋጋ ነው።
22ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ ውርስ ትቶ ያልፋል፤
የኀጢአተኞች ሀብት ግን ለጻድቃን ይከማቻል።
23የድኾች ዕርሻ የተትረፈረፈ ምርት ያስገኛል፤
የፍትሕ መጓደል ግን ጠራርጎ ይወስደዋል።
24በአርጩሜ ከመቅጣት የሚሳሳለት ልጁን ይጠላል፤
የሚወድደው ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል።
25ጻድቅ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤
የክፉዎች ሆድ ግን እንደ ተራበ ይኖራል።
Copyright information for
AmhNASV