Proverbs 16
1የልብ ዕቅድ የሰው ነው፤የአንደበት መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
2ለሰው መንገዱ ሁሉ ንጹሕ መስሎ ይታየዋል፤
መነሻ ሐሳቡ ግን በእግዚአብሔር ይመዘናል።
3የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤
ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል።
4 እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ለራሱ ዐላማ ሠርቷል፤
ክፉዎችንም እንኳ ለጥፋት ቀን አዘጋጅቷል።
5 እግዚአብሔር በልብ የሚታበዩትን ሁሉ ይጸየፋል፤
እነርሱም ከቅጣት እንደማያመልጡ በርግጥ ዕወቅ።
6በፍቅርና በታማኝነት ኀጢአት ይሰረያል፤
እግዚአብሔርን በመፍራት ሰው ከክፋት ይርቃል።
7የሰው መንገድ እግዚአብሔርን ደስ ሲያሰኘው፣
ጠላቶቹ እንኳ አብረውት በሰላም እንዲኖሩ ያደርጋል።
8ከጽድቅ ጋር ጥቂቱ ነገር፣
በግፍ ከሚገኝ ብዙ ትርፍ ይሻላል።
9ሰው በልቡ መንገዱን ያቅዳል፤
እግዚአብሔር ግን ርምጃውን ይወስንለታል።
10የንጉሥ ከንፈሮች እንደ አምላክ ቃል ይናገራሉ፤
አንደበቱ ፍትሕን ያዛባ ዘንድ አይገባም።
11ሐቀኛ መስፈሪያና ሚዛን ከእግዚአብሔር ናቸው፤
በከረጢት ውስጥ ያሉት መመዘኛዎችም ሁሉ ሥራዎቹ ናቸው።
12ክፋትን ማድረግ ለነገሥታት አስጸያፊ ነው፤
ዙፋን የሚጸናው በጽድቅ ነውና።
13ነገሥታት በታማኝ ከንፈሮች ደስ ይላቸዋል፤
እውነት የሚናገረውን ሰው ይወድዱታል።
14የንጉሥ ቍጣ የሞት መልእክተኛ ነው፤
ጠቢብ ሰው ግን ቍጣውን ያበርዳል።
15የንጉሥ ፊት ሲፈካ ሕይወት አለ፤
በጎነቱም ዝናብ እንዳዘለ የበልግ ደመና ነው።
16ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣
ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!
17የቅኖች ጐዳና ከክፋት የራቀ ነው፤
መንገዱንም የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል።
18ትዕቢት ጥፋትን፣
የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።
19በተዋረደ መንፈስ ከተጨቈኑት ጋር መሆን፣
ከትዕቢተኞች ጋር ብዝበዛን ከመካፈል ይሻላል።
20ምክርን የሚሰማ ይለመልማል፤
በእግዚአብሔርም የሚታመን ቡሩክ ነው።
21ልባቸው ጠቢብ የሆነ አስተዋዮች ይባላሉ፤
ደስ የሚያሰኙ ቃላትም ዕውቀትን ያዳብራሉ። ▼
▼ወይም ቃላትም ተደማጭነት ያስገኛሉ
22ማስተዋልን ገንዘብ ላደረጋት የሕይወት ምንጭ ናት፤
ቂልነት ግን በተላሎች ላይ ቅጣት ታመጣባቸዋለች።
23የጠቢብ ሰው ልብ አንደበቱን ይመራል፤
ከንፈሮቹም ዕውቀትን ያዳብራሉ። ▼
▼ወይም አንደበቱን አሳማኝ ያደርጋሉ
24ደስ የሚያሰኝ ቃል የማር ወለላ ነው፤
ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ ነው።
25ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤
በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።
26ሠራተኛን የዕለት ጕርስ ፍላጎቱ ታታሪ ያደርገዋል፤
ራቡም ይገፋፋዋል።
27ወራዳ ሰው ክፋትን ያውጠነጥናል፤
ንግግሩም እንደሚለበልብ እሳት ነው።
28ጠማማ ሰው ጠብን ይዘራል፤
ሐሜተኛም የቅርብ ወዳጆችን ይለያያል።
29ክፉ ሰው ባልንጀራውን ያባብለዋል፤
መልካም ወዳልሆነውም መንገድ ይመራዋል።
30በዐይኑ የሚጠቅስ ሰው ጠማማነትን ያውጠነጥናል፤
በከንፈሩ የሚያሽሟጥጥም ወደ ክፋት ያዘነብላል።
31ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤
የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው።
32ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣
ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጕልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል።
33ዕጣ በጕያ ውስጥ ይጣላል፤
ውሳኔው በሙሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
Copyright information for
AmhNASV