Proverbs 23
1ከገዥ ጋር ለመብላት በምትቀመጥበት ጊዜ፣በፊትህ ያለውን በሚገባ ▼
▼ወይም ማን መሆኑን
አስተውል፤2ስግብግብም ብትሆን እንኳ፣
በጕረሮህ ላይ ካራ አጋድምበት፤
3የእርሱ ጣፋጭ መብል አያስጐምጅህ፤
ምግቡ አታላይ ነውና።
4ሀብት ለማግኘት ስትል ራስህን አታድክም፤
ሐሳብህን የመግታት ጥበብ ይኑርህ።
5በሀብት ላይ ዐይንህን ብትጥል፣
ወዲያው ይጠፋል፤
ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር፣ በርግጥ ክንፍ አውጥቶ ይበርራል።
6የሥሥታምን ምግብ አትብላ፤
ጣፋጭ መብሉም አያስጐምጅህ፤
7ሁልጊዜ ስለ ዋጋ የሚያሰላ ሰው ነውና፤ ▼
▼ወይም በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና ወይም ግብዣ አዘጋጅቶ
“ብላ፣ ጠጣ” ይልሃል፤
ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም።
8የበላሃት ትንሿ እንኳ ታስመልስሃለች፤
የምስጋና ቃልህንም ከንቱ ታደርጋለህ።
9ከጅል ጋር አትነጋገር፤
የቃልህን ጥበብ ያንኳስሳልና።
10የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ፤
አባት የሌላቸውንም ልጆች መሬት አትግፋ፤
11ታዳጊያቸው ብርቱ ነውና፤
እርሱ ይፋረድላቸዋል።
12ልብህን ለምክር፣
ጆሮህንም ለዕውቀት ቃል ስጥ።
13ልጅን ከመቅጣት ወደ ኋላ አትበል፤
በአርጩሜ ብትገርፈው አይሞትም።
14በአርጩሜ ቅጣው፤
ነፍሱንም ከሞት ▼
▼ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል
አድናት።15ልጄ ሆይ፤ ልብህ ጠቢብ ቢሆን፣
የእኔም ልብ ሐሤት ያደርጋል፤
16ከንፈሮችህ ትክክሉን ቢናገሩ፣
ውስጣዊ ሁለንተናዬ ሐሤት ያደርጋል።
17ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤
ነገር ግን ዘወትር እግዚአብሔርን ለመፍራት ትጋ።
18ለነገ ርግጠኛ አለኝታ ይኖርሃል፤
ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።
19ልጄ ሆይ አድምጥ፤ ጠቢብም ሁን፤
ልብህም ከትክክለኛው መንገድ አይውጣ።
20ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣
ሥጋ ከሚሰለቅጡ ጋር አትወዳጅ፤
21ሰካራሞችና ሆዳሞች ድኾች ይሆናሉና፤
እንቅልፋምነትም ቡትቶ ያለብሳቸዋል።
22የወለደህን አባትህን አድምጥ፤
እናትህንም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።
23እውነትን ግዛት እንጂ አትሽጣት፤
ጥበብን፣ ተግሣጽንና ማስተዋልን ገንዘብህ አድርግ።
24የጻድቅ ሰው አባት እጅግ ደስ ይለዋል፤
ጠቢብ ልጅ ያለውም በእርሱ ሐሤት ያደርጋል።
25አባት እናትህ ደስ ይበላቸው፤
ወላጅ እናትህም ሐሤት ታድርግ።
26ልጄ ሆይ፤ ልብህን ስጠኝ፤
ዐይኖችህም ከመንገዴ አይውጡ፤
27ዘልዛላ ሚስት ጠባብ ጕድጓድ፣
አመንዝራም ሴት ዐዘቅት ናትና፤
28እንደ ወንበዴ ታደባለች፤
በሰዎችም መካከል ወስላቶችን ታበዛለች።
29ዋይታ የማን ነው? ሐዘንስ የማን ነው?
ጠብ የማን ነው? ብሶትስ የማን ነው?
በከንቱ መቍሰል የማን ነው? የዐይን ቅላትስ የማን ነው?
30የወይን ጠጅ በመጠጣት ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ ነው፤
እየዞሩ ድብልቅ የወይን ጠጅ ለሚቀማምሱ ሰዎች ነው።
31መልኩ ቀይ ሆኖ፣
በብርጭቆ ውስጥ ሲያንጸባርቅ፣
ሰተት ብሎ በሚወርድበትም ጊዜ፣ ወደ ወይን ጠጅ ትክ ብለህ አትመልከት።
32በመጨረሻው እንደ እባብ ይነድፋል፤
እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል።
33ዐይኖችህ እንግዳ ነገር ያያሉ፤
አእምሮህም ይቀባዥራል።
34በባሕር ላይ የተኛህ፣
በመርከብ ምሰሶ ጫፍ ላይ የተጋደምህ ትመስላለህ።
35አንተም፣ “መቱኝ፤ አልተጐዳሁም፤
ደበደቡኝ፤ አልተሰማኝም፤
ታዲያ፣ ሌላ መጠጥ እንዳገኝ፣
መቼ ነው የምነቃው?” ትላለህ።
Copyright information for
AmhNASV