Proverbs 25
የሰሎሞን ተጨማሪ ምሳሌዎች
1እነዚህ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዷቸው ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፦2ነገርን መሰወር ለእግዚአብሔር ክብሩ ነው፤
ነገርን ፈልፍሎ ማውጣት ግን ለነገሥታት ክብራቸው ነው።
3ሰማያት ከፍ ያሉ እንደ ሆኑ፣ ምድርም ጥልቅ እንደ ሆነች ሁሉ፣
የነገሥታትም ልብ እንደዚሁ አይመረመርም።
4ከብር ዝገትን አስወግድ፤
አንጥረኛውም ንጹሕ ነገር ▼
▼ወይም ጽዋ
ያገኛል፤5ክፉን ከንጉሥ ፊት አርቅ፤
ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች።
6በንጉሥ ፊት ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤
በታላላቆች መካከል መገኘትም አይመርህ፤
7በትልቅ ሰው ፊት ከሚያዋርድህ፣
ራሱ፣ “ወደዚህ ከፍ በል” ቢልህ ይሻላልና።
በዐይንህ ያየኸውን ሁሉ፣
8ወደ ፍርድ አደባባይ በችኰላ አታውጣው፤ ▼
▼ወይም ዐይንህን የጣልህበትን የከበረ ሰው፣ 8 …አትውጣ
ባልንጀራህ ካሳፈረህ፣
ኋላ ምን ይውጥሃል?
9ስለ ራስህ ጕዳይ ከባልንጀራህ ጋር በምትከራከርበት ጊዜ፣
የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ፤
10ያለዚያ ይህን የሚሰማ ያሳፍርሃል፤
አንዴ የጠፋውን ስምህንም ፈጽሞ መመለስ አትችልም።
11ባግባቡ የተነገረ ቃል፣
በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው።
12የጠቢብ ሰው ዘለፋ ለሚሰማ ጆሮ፣
እንደ ወርቅ ጕትቻ ወይም እንደ ጥሩ የወርቅ ጌጥ ነው።
13በመከር ጊዜ የበረዶ ቅዝቃዜ ለሰስ እንደሚያደርግ ሁሉ፣
ታማኝ መልእክተኛም ለላኩት እንደዚሁ ነው፤
የጌቶቹን መንፈስ ያሳርፋልና።
14የማይለግሰውን ስጦታ እቸራለሁ ብሎ ጕራ የሚነዛ ሰው፣
ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው።
15በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል፤
ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል።
16ማር ስታገኝ በልክ ብላ፤
ከበዛ ያስመልስሃል።
17ወደ ባልንጀራህ ቤት እግር አታብዛ፤
ታሰለቸውና ይጠላሃል።
18በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር፣
እንደ ቈመጥ፣ እንደ ሰይፍና እንደ ተሳለ ፍላጻ ነው።
19በመከራ ጊዜ በወስላታ ሰው መተማመን፣
በተበላሸ ጥርስና በሰለለ እግር እንደ መታመን ነው።
20ላዘነ ልብ የሚዘምር፣
በብርድ ቀን ልብሱን እንደሚያወልቅ፣
ወይም በሶዳ ላይ እንደ ተጨመረ ሆምጣጤ ነው።
21ጠላትህ ቢራብ አብላው፤
ቢጠማም ውሃ አጠጣው።
22ይህን በማድረግህም፣ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ፤
እግዚአብሔርም ዋጋህን ይከፍልሃል።
23የሰሜን ነፋስ ዝናብ እንደሚያመጣ ሁሉ፣
ሐሜተኛ ምላስም ቍጡ ፊት ታስከትላለች።
24ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር፣
በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል።
25ከሩቅ የሚመጣ መልካም ዜና፣
የተጠማችን ነፍስ እንደሚያረካ ቀዝቃዛ ውሃ ነው።
26ለክፉ ሰው የሚንበረከክ ጻድቅ፣
እንደ ደፈረሰ ምንጭ ወይም እንደ ተበከለ የጕድጓድ ውሃ ነው።
27ከመጠን በላይ ማር መብላት ጥሩ አይደለም፤
የራስንም ክብር መሻት አያስከብርም።
28ራሱን የማይቈጣጠር ሰው፣
ቅጥሯ እንደ ፈረሰ ከተማ ነው።
Copyright information for
AmhNASV